መንግስት የውጭ ባንኮችን ወደ ኢትዮጵያ ለማስገባት የፖሊሲ ማሻሻያ እንደሚያደርግ ጠ/ሚ ዐቢይ ገለፁ
የኢትዮጵያ ባንኮች አጠቃላይ ሀብት 2 ትሪልየን ብር መድረሱን ገልፀዋል
ኢትዮጵያ በ6 ወራ ከውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት 1 ነጥብ 63 ቢሊየን ዶላር አግኝታለች
ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ቀርበው ከምክር ቤቱ አባላት ለቀረቡላቸው ጥያቄዎች ምለሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራያቸው የኢኮኖሚ ጉዳዮችን ያነሱ ሲሆን፤ ከእነዚህም የባንኮች ጉዳይ አንዱ ነበር።
በዚህም የኢትዮጵያ ባንኮች ሀብት እያደረገ መምጣቱን አንስተው፤ ባለፉት ስድስት ወራት ብቻ የባንኮች የሀብት ከነበረበት 1.8 ትሪሊየን ብር ወደ በ2 ትሪሊየን ማደጉን አስታውቀዋል።
የባንኮች ተቀማጭ ሀብትም ባለፈው ዓመት ከነበረበት 1 ነጥብ 3 ትሪሊየን ባለፈው ስድስት ወራት ወደ 1 ነጥብ 5 ትሪሊየን ብር ማደጉን አስታውቀዋል።
የባለድርሻዎች የሀብት መጠንም እንዲሁ ጭማሪ አሳይቷል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በዚህም የአክሲዮች ባለድርሻዎች ሀብት 159 ቢሊየን ብር መድረሱንም አስታውቀዋል።
የባንኮች የቅርጫፍ መጠን ባለፈው ስድስት ወር በተሰራው ስራ ከ6 ሺህ 700 ወደ 7 ሺህ 400 መድረሱንም ከፍ ማት መቻሉንም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያስታወቁት።
የኢትዮጵያ ባንኮች ላለፉት 20 ዓመታት ብቻቸውን የሚሰሩበትን እድል አግኝተው ቆይተዋል ያሉት ጠቅላይ ሚኒሰትር ዐቢይ፤ አሁን ግን ይህንን ማስቀጠል አይቻልም፤ ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ፣ ተጨማሪ ሀብት ስለሚያስፈልግ የውጭ ባንኮች መምጣታቸው አይቀርም ብለዋል።
“ባንኮች በቴክኖሎጂ እና በዘመናዊ አሰራር ራሳቸውን በማደራጀት ከፍ ላለ ውድድር ራሳቸውን ማዘጋጀት አለባቸው” ያሉ ሲሆን፤ መንግስት የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ የፖሊሲ ማሻሻያ ለማድረግ እየተዘጋጀ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በማብራራያቸው በስድስት ወራት የገነኘውን ገቢ ያነሱ ሲሆን፤ በዚህም ባለፉት 6 ወራት መንግስት 185 ነጥብ 8 ቢሊየን በር ለመሰብሰብ አቅዶ 171 ነጥብ 3 ቢሊየን መሰብሰብ መቻሉን አስታውቀዋል።
ይህም የአቅዱ 92 በመቶ መሆኑን ያስታወቁት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ገቢ በተወሰነ መጠን አድጎ መጪ ግን በጣም በመጨመሩ የበጀት ጉድለቱ መስፋቱን አስታውቀዋል።
ከወጪ እና ገቢ ንግድ ጋር በያያዘም፤ ባለፉት ስድስት ወራ የኢትዮጵያ የወጪ ንግድ (ኤክስፖርት) በ25 በመቶ እድገት ማሳየቱን የገለፁ ሲሆን፤ ከዚህም የግብርና ምርቶች ከፍተኛ ድርሻ እንደሚይዝ አስታውቀዋል።
በዚህም በ6 ወር ውስጥ ወደ ውጪ ከተላከ ምርት ወደ 2 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር ገደማ እንደተገኘም ነው ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ያስታወቁት
የገቢ ንግድ (ኢምፖርት) ከዚህ በፊት ቅናሽ ቢያሳይም፤ አሁን ግን ጭማሪ አሳይቷል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ይህም በ6 ወራት በ25 በመቶ ጭማሪ አሳይቷል ብለዋል።
ከዚሁ ጋር በተያያዘም ከውጭ ከሚገቡ ምርቶች ውስጥ አንድ ቢሊየን ዶላር ያህል በሀገር ውስጥ መተካት መቻሉን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ተናግረዋል።
ከንግድ እና ከኢንቨስትመንት ጋር በተያያዘም፤ ባለፉት ስድስት ወራት 1 ነጥብ 63 ቢሊየን የአሜሪካ ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመን መገኘቱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
ይህም ካፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር በ23 በመቶ ጭማሪ ያለው መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስታውቀዋል።
የኑሮ ውድነትን በተመለከት አሁን ላይ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው የኑሮ ውድነት ዋነኛው መንስዔ ከምግብ ነክ ሸቀጦች ጋር የሚያያዝ መሆኑንም አስታውቀዋል።
የፍላጎት መጨመርም አንዱ ችግር መሆኑን ጠቅሰው፤ ለዚህም አንዱ የህዝብ ቁጥር መጨመር ነው፤ የወሊድ ምጣኔያችንን ማስተካከል ይገባል ብለዋል።
በዓለም አቀፍ ገበያ ያለው የሸቀጦች እና የነዳጅ ዋጋ መጨመርም ለኑሮ ውድነቶ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንዳለውም አስታውቀዋል።
መንግስት የዋጋ ንረቱን ለማረጋጋት ባለፈው ስድስት ወር ብቻ በ2 ነጥብ 6 ቢሊየን ዶላር የምግብ ሸቀጦችን በመግዛት ወደ ሀገር ውስጥ ማስገባቱን ገልጸዋል።
ለዘይት አምራቾች ከተሰጣቸው በተጫመሪ የውጭ ምንዛሪ ኮታ ተሰጥቶ እንዲገባ መደረጉን እንዲሁም ስንዴ በብዛት እየተመረተ ቢሆንም እጥረት እንዳይፈጠር ግዢ ተፈፅሞ ወደ ሀገር ውስጥ መግባቱን አስታውቀዋል።