የባንኩ ገዢ የሞባይል አገልግሎት የሚሰጡ የውጭ ተቋማት በቅርብ ጊዜ የአገልግሎት ፈቃድ ሊያገኙ እንደሚችሉ ተናግረዋል
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የኢትዮጵያ ባንኮች ከውጭ ባንኮች ለሚኖር ውድድር ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ ጥሪ አቀረበ፡፡
ጥሪው በባንኩ ገዢ ይናገር ደሴ (ዶ/ር) የቀረበ ነው፡፡
ዶ/ር ይናገር ደሴ ይህን ያሉት ዛሬ ቅዳሜ ሰኔ ቀን 2014 ዓ/ም በተካሄደ የአማራ ባንክ ይፋዊ የስራ ማስጀመሪያ ስነ ስርዓት ላይ ነው፡፡
መንግስት የውጭ ባንኮችን ወደ ኢትዮጵያ ለማስገባት የፖሊሲ ማሻሻያ እንደሚያደርግ ጠ/ሚ ዐቢይ ገለፁ
በስነ ስርዓቱ ወደ ገጠሩ ማህበረሰብ በመድረስና ከፍተኛ የአክስዮን ድርሻን በመሸጥ እንዲሁም ከፍተኛ የተከፈለ ካፒታል ይዞ የባንክ ኢንዱስትሪውን በመቀላቀል የአማራ ባንክ ቀዳሚው ነው ያሉት ዶ/ር ይናገር በቴክኖሎጂ እና በአገልግሎት አሰጣጥ ተወዳዳሪ በመሆን ቀዳሚ መሆን እንዲችል ራሱን ያዘጋጅ ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ይህ ከሃገር ውስጥ ብቻም ሳይሆን ወደ ኢትዮጵያ እንደሚገቡ ከሚታሰቡ የውጭ ባንኮች ጋር ጭምር ለመወዳደር እንደሚያስችል ነው የተናገሩት፡፡
እንደሚገቡ ከሚጠበቁት የውጭ ባንኮች ጋር ለመወዳደር ትልቅ ዝግጅት ይጠብቀናልም ብለዋል የብሔራዊ ባንክ ገዢው፡፡
ለዚህም አማራ ባንክን ጨምሮ ሌሎች የኢትዮጵያ ባንኮች ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ኢትዮጵያ ቢትኮይንን መሰል የዲጂታል መገበያያ ገንዘቦችን አገደች
አማራ ባንክ ይህን የሚያደርግና የቁጠባ ገንዘብ አቅሙን ለማሳደግ የሚችል ከሆነ በአጭር አመታት ውስጥ ከፍተኛ ደረጃ ሊደርስ እንደሚችል ያላቸውን ግምት አስቀምጠዋል፡፡
60 ሚሊዮን ገደማ ኢትዮጵያውያን የተንቀሳቃሽ ስልክ (ሞባይል) ተጠቃሚ መሆናቸውን በማስታወስም ባንኩ የተፋጠነ የሞባይል አገልግሎትን በየደረጃው ለመስጠት እንዲችልም መክረዋል፡፡
የሞባይል አገልግሎት በገጠርም በከተማም እንዲጀመር መደረጉን ያነሱት ዶ/ር ይናገር የሞባይል አገልግሎት የሚሰጡ የውጭ ተቋማት በቅርብ ጊዜ የአገልግሎት ፈቃድ ሊያገኙ እንደሚችሉ ተናግረዋል፤ በአሁኑ ወቅት ቴሌ ብር ብቻ አገልግሎቱን እየሰጠ እንደሚገኝ በመጠቆም፡፡
“በመሆኑም አማራ ባንክ ቅርንጫፎችን ከመክፈት በዘለለ በቴክኖሎጂ ላይ ኢንቨስት ማድረግ ወደ ከፍታ ሊወስደው እንደሚችል አስባለሁ”ም ነው ዶ/ር ይናገር ያሉት፡፡
6 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር የተከፈለ ካፒታል ኖሮት ዛሬ ስራ የጀመረው አማራ ባንክ ከ185 ሺ ገደማ ባለ አክስዮኖች እንዳሉት በስነ ስርዓቱ ተገልጿል፡፡