ብሔራዊ ባንክ የሀገር ውስጥ ባንኮች ከውጭ ባንኮች ለሚገጥማቸው ውድድር ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ መክሯል
የኢትዮጵያ መንግስት የውጭ ባንች ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ ገብተው ኢንቨስት እንዲያደርጉ ወስኗል፡፡
የሚኒስትሮች ምክርቤት ባለፈው ሳምንት የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ እንዲገቡ በቀረበው ረቂቅ ፖሊሲ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏ፡፡
መንግስት የባንክ ዘርፉን ለውጭ ባንኮች ክፍት የሚያደርገው ኢትዮጵያ ከአለምአቀፍ ገበያ ጋር ትስስር እንድትፈጥር፣ የውጭየ ምንዛሬ ልውውጥን ለመጨመር እና አለምአቀፍ ተወዳዳሪነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት ለማምጣት ነው ብሏል።
ነገርግን ውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ መምጣት የሚያስከትለው ጉዳት እና ጥቅም እንዳለው የምጣኔ ሀብት ባለሙያዎች ይናገራሉ፡፡
የምጣኔ ሀብት ፖሊሲ ተመራማሪ ደግዬ ጎሹ (ዶ/ር) ለአል ዐይን አማርኛ እንደተናገሩት የመንግስት ውሳኔ ሀገራዊ ኢኮኖሚው ባልተረጋጋበት ሁኔታ ኢኮኖሚውን ለውጭ ባንኮች ክፍት ማድረጉ ትክክል አይደለም፡፡
መንግስት የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ እንዲገቡ ከመፍቀዱ በፊት የሀገር ውስጥ ባንኮች ለውድድር ዝግጁ እንዲሆኑ ፖሊሲዎችን በማውጣት ማለማመድ ነበረበት ይላሉ ደግዬ ጎሹ (ዶ/ር)፡፡
የኢትዮጵያ ባንኮች ከደንበኞቻቸው ብዙ ገንዘብ በትንሽ ወለድ እየተቀበሉ መልሰው በከፍተኛ የብድር መጠን በመስጠት በዓመት በቢሊዮን እና ሚሊዮኖች የሚቆጠር ከፍተኛ ትርፍ እንዲያገኙ ሲደረግ መቆየቱንም ዶክተር ደግዬ ተናግረዋል፡፡
የውጭ ባንኮች በዚህ ሁኔታ ውስጥ ወደ ኢትዮጵያ ከገቡ በልዩ ጥበቃ ትርፍ ሲሰበስቡ የቆዩ ሀገር በቀል ባንኮች እንደበፊቱ በዓመት ከፍተኛ ትርፍ ማግኘታቸው ይቀራል፣ ቀስ በቀስም ወደ መክሰም እና ከውድድር ውጪ የመሆን አደጋ አለባቸውም ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ባንኮች ራሳቸውን ለዓለም አቀፍ ባንኮች ውድድር ዝግጁ ባላደረጉበት ሁኔታ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች ክፍት መደረጉ ባልተረጋጋው የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ላይ ተጨማሪ ፈተና ይዞ መምጣቱ አይቀሬ መሆኑንም አንስተዋል፡፡
ባለሙያው ሀገራዊ ኢኮኖሚው ባልተረጋጋበት ሁኔታ የተለየ ጥቅም ሊያገኝ የሚችል ደንበኛ ሊኖር አይችልም ብለዋል፡፡
“መንግስት የውጭ ሀገራት ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ገብተው እንዲሰሩ ያሳለፈውን ውሳኔ በእልልታ ነው የተቀበልኩት፣ በኢትዮጵያ የመንግስታት ውሳኔዎች ታሪክ ካሳለፏቸው ውሳኔዎች ውስጥ እንደ አሁኑ ውሳኔ የደገፍኩት የመንግስት ውሳኔ የለም፡፡“ያሉን ደግሞ ሌላኛው የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አቶ ሸዋፈራሁ ሽታሁን ናቸው፡፡
አቶ ሸዋፈራሁ በቡድን እና በብሄር እየተደራጁ ትናንሽ ባንኮችን በማቋቋም ዓለም አቀፍ የባንክ ኢንዱስትሪ ውስጥ ተወዳዳሪ መሆን አይቻልም ብለዋል፡፡
የመንግስት ውሳኔ “ተጨማሪ ገንዘብ ወደ ኢትዮጵያ እንዲመጣ ከማድረጉ ባለፈ በተበጣጠሰ መንገድ እየተንቀሳቀሱ ያሉ ሀገር በቀል ባንኮች ለህልውናቸው ሲሉ ወደ ውህደት እንዲመጡ ያስገድዳቸዋል” ሲሉም አቶ ሸዋፈራሁ ገልጸዋል፡፡
ውሳኔውን ተከትሎ የውጭ ሀገራት ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ሲገቡ እና አገልግሎት መስጠት ሲጀምሩ የሀገር ውስጥ ባንኮች ለመወዳደር ሲሉ ውህደት ሲፈጥሩ ጠንካራ እና ተወዳዳሪ የሆነ ኢትዮጵያዊ የባንክ ተቋም እንዲመሰረት ያደርጋልም ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ለአንድ የፈጠራ ስራ ገንዘብ እንደማግኘት ከባድ ፈተና የለም የሚሉት አቶ ሸዋፈራሁ ውሳኔውን ተከትሎ ግን ባንኮች የበለጠ ሀሳብ ወዳላቸው ሰዎች እንዲመጡ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡
አቶ ሸዋፈራሁ አክለውም በኢትዮጵያ ከፍተኛ የፋይናንስ እጥረት እንዳለ ገልጸው ባንኮቻችን በከፍተኛ ወለድ ለተበዳሪዎች እየሰጡት ያለውን አገልግሎት ለመወዳደር ሲሉ ወደ እንደሚቀንሱ ገልጸዋል፡፡ይህ መሆኑ ደግሞ ወደ ኢንቨስትመንት የሚገቡ አልሚዎችን ቁጥር ስለሚያሳድገው ለኢኮኖሚው ተጨማሪ አቅም ይሆናል ብለዋል ባለሙያው፡፡
የመንግስት አዲስ ውሳኔ ባንኮቻችንን ሳይወዱ በግድ ተወዳዳሪ ለመሆን ሲሉ አገልግሎቶቻቸውን ያሻሽላሉ፣ ሰው ሃይል እና ቴክኖሎጂ ልማት ላይ እንዲያተኩሩ ያደርጋል የሚሉት አቶ ሸዋፈራሁ ይሄንን ካላደረጉ ግን የመዋጥ አደጋ አለባቸው ሲሉ አሳስበዋል፡፡
መንግስት ቀድሞ ነው ስራ የጀመረው፣ ከአምስት ዓመት በፊት የቢዝነስ እና ኮንስትራክሽን ባንክ ከንግድ ባንክ ጋር መርጅ አድርጓል፡፡
የኢትዮጵያ ብሄራዊ ባንክ ገዢ ይናገር ደሴ (ደ/ር) ከዚህ በፊት በተደጋጋሚ ሀገር በቀል ባንኮች ከውጭ ባንኮች ጋር ለሚኖረው ውድድር ራሳቸውን ለውድድር እንዲያዘጋጁ ሲያሳስቡ መቆየታቸው ይታወሳል፡፡
ዋና ገዢው ከአንድ ወር በፊት ከባንኮች ፕሬዝዳንቶች ጋር በነበራቸው የውይይት መድረክ ላይ ያልተደራጁ 20 እና 30 ባንኮች ከሚኖሩን ይልቅ ሁለት እና ሶስት ጠንካራ እና ተወዳዳሪ ባንኮች ቢኖሩን እንመርጣለን ብለዋል፡፡