የምክር ቤት አባላት፤ የውጭ ባንኮች እንዲገቡ መፈቀዱ የሀገር ውስጥ ባንኮች ላይ ተጽእኖ ሊኖረው እንደሚችል ስጋታቸውን ገልጸዋል
ኢትዮጵያ የውጭ ሀገራት ባንኮች ሀገር ውስጥ ገብተው እንዲሰሩ ፈቀደች።
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው መደበኛ ስብሰባው የውጭ ባንኮች በሀገር ውስጥ ገብተው እንዲሰሩ የሚፈቅድ አዋጅ አስጽድቋል።
ዛሬ የፀደቀው የባንክ ሥራ ረቂቅ አዋጅ የውጭ ባንኮችን በሀገር ውስጥ በማሳተፍ ዘርፉን ለውጭ ኢንቨስትመንት ክፍት በማድረግ የባንኮችን ተወዳዳሪነት እና ውጤታማነት የሚያሻሽል መሆኑን የፕላን፤ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ደሳለኛ ወዳጄ አብራተዋል።
አዋጁ ለኢኮኖሚው ዕድገት ፋይዳው የጎላ መሆኑንየ ቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ ማስረዳታቸውን ከምክር ቤቱ ጽህፈት ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
የምክር ቤት አባላት በአዋጁ ላይ ያላቸው ስጋት እና ጥያቄ ያቀረቡ ሲሆን፤ “በቂ የሆነ ቅድመ ዝግጅት ሳይደረግ የውጭ ባንኮች ወደ ሀገር ውስጥ ገብተው እንዲሰሩ ፈቃድ መስጠቱ የሀገር ውስጥ ባንኮች ላይ ተጽእኖ ሊኖረው ይችላል” ሲሉ ስጋታቸውን ገልጸዋል።
በተለይ የግል ባንኮች ላይ ያለውን ተወዳዳሪነት እና አቅምን ያማከለ አዋጅ መሆን እንዳለበት የምክር ቤቱ አባላት አሳስበዋል፡፡
ብሔራዊ ባንክ የውጭ ባንኮችን ለመቆጣጠር እና ለማስተዳደር የሚያስችል ዘመኑን የዋጀ የዓሰራር ስርዓት መዘርጋት እንደሚጠበቅበትም የምክር ቤት አባላት አሳስበዋል፡፡
የውጭ ባንኮች በሀገር ውስጥ የሚያፈሩትን ገንዘብ ወደ ሌላ ሀገራት እንዳያሸሹ ብሔራዊ ባንክ መከታተል እና መቆጣጠር እንዳለበት የምክር ቤት አባላት አመላክተዋል፡፡
የውጭ ባንኮች ከዲጅታል አሰራር ጋር በተያያዘ የሀገርን ሉአላዊነትና ደህንነት በጠበቀ መልኩ የፋይናንስ ስርአቱ እንዲመራ ብሔራዊ ባንክ በትኩረት መስራት እንዳለበት የምክር ቤቱ አባላት አሳስበዋል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምህረቱ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፤ “የውጭ ባንኮች ወደ ሀገር ውስጥ ይገባሉ ማለት በጋር እና በሽርክና ጭምር ከሀገር ውስጥ ባንኮች ጋር በትብብር የሚሰሩ መሆኑን መረዳት ይገባል” ሲሉ አስረድተዋል፡፡
የሀገር ውስጥ ባንኮችም አቅማቸውን በማጎልበት ተወዳደሪ ለመሆን ሰብሰብ ብለው የፋይናንስ አቅማቸውን ማጠናከር ይጠበቅባቸዋል ሲሉ አስገንዝበዋል፡፡
ባንኮችን ከመቆጣጠር እና ከማስተዳደር አንጻር በህግ የተሰጠውን ኃላፊነት ብሔራዊ ባንክ በአግባቡ የሚወጣ መሆኑንም አቶ ማሞ ምህረቱ ገልጸዋል፡፡
በኢትዮጵያ የሚገኙ የተለያዩ የኢኮኖሚ ዘርፎች ባለፉት አመታት ለውጭ ኩባንያዎች ተሳትፎ ዝግ ሆነው የቆዩ ናቸው።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ ግን መንግስት የባንኩን ዘርፍ ከፍት እንደሚያደር በተደጋጋሚ ማሰወቁ እና የሀገር ውስጥ ባኮችም ራሳውቸው ለውድድር እንዲያዘጋጁ ሲያሳስብ መቆየቱ አይዘነጋም።
መንግስት የባንክ ዘርፉን ለውጭ ባንኮች ክፍት የሚያደርገው ኢትዮጵያ ከአለምአቀፍ ገበያ ጋር ትስስር እንድትፈጥር፣ የውጭየ ምንዛሬ ልውውጥን ለመጨመር እና አለምአቀፍ ተወዳዳሪነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት ለማምጣት ነው ብሏል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከዚህ ቀደም በፓርላማ ቀርበው ባደረጉት ንግግር፤ የኢትዮጵያ ባንኮች ላለፉት 20 ዓመታት ብቻቸውን የሚሰሩበትን እድል አግኝተው ቆይተዋል፤ አሁን ግን ይህንን ማስቀጠል አይቻልም ማታው ይታወሳል።
ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ፣ ተጨማሪ ሀብት ስለሚያስፈልግ የውጭ ባንኮች መምጣታቸው አይቀርም ብለውም ነበር።
“ባንኮች በቴክኖሎጂ እና በዘመናዊ አሰራር ራሳቸውን በማደራጀት ከፍ ላለ ውድድር ራሳቸውን ማዘጋጀት አለባቸው” ሲሉም በወቅቱ አሳስበው ነበር።