መንግስት የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ ኢንቨስት የሚያደርጉበት ፖሊሲ ስራ ላይ እንዲውል ወሰነ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የውጭ ባንኮች መግባታቸው አይቀርም ብለው ነበር
ብሔራዊ ባንክ የሀገር ውስጥ ባንኮች ከውጭ ባንኮች ለሚኖረው ወድድር ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ ማሳሰቡ ይታወሳል
የኢትዮጵያ መንግስት የሚኒስትሮች ምክርቤት ዛሬ እለት የውጭ ባንኮች በኢትዮጵያ የባንክ ዘርፍ እንዲገቡ በቀረበው ረቂቅ ፖሊሲ ላይ ተወያይቶ ውሳኔ ማሳለፉን አስታውቋል።
የጠቅላይ ሚኒስትር ጸ/ቤት ባወጣው መግለጫ የሚኒስትሮች ም/ቤት በረቂቅ ፖሊሲው ላይ ከተወያየ በኋላ ስራ ላይ እንዲውል ወሰኗል።
መንግስት የባንክ ዘርፉን ለውጭ ባንኮች ክፍት የሚያደርገው ኢትዮጵያ ከአለምአቀፍ ገበያ ጋር ትስስር እንድትፈጥር፣ የውጭየ ምንዛሬ ልውውጥን ለመጨመር እና አለምአቀፍ ተወዳዳሪነት ያለው የኢኮኖሚ እድገት ለማምጣት ነው ብሏል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐበይ አህመድ ባለፈው ጥር ወር በህዝብ ተወካዮች ም/ቤት በቀረቡበት ወቅት የውጭ ባንኮች ወደ ኢትዮጵያ ገበያ እንዲገቡ ፖሊሲ እየተዘጋጀ መሆኑን ተናግረው ነበር።
ጠቅላይ ሚኒሰትር ዐቢይ የኢትዮጵያ ባንኮች ለ20 አመታት ብቻቸውን መስራታቸውን እና ይህንን ማስቀጠል አይቻልም ሲሉ በወቅቱ መናገራቸው ይታወሳል።
ተጨማሪ የውጭ ምንዛሪ እና ተጨማሪ ሀብት ስለሚያስፈልግ የውጭ ባንኮች መምጣታቸው አይቀርም ብለው ነበር ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ የሀገር ውስጥ ባንኮች ከውጭ ባንኮች ለሚኖረው ወድድር ራሳቸውን እንዲያዘጋጁ አሳስቧል።
የሀገር ውስጥ ባንኮች የውጭ ባንኮች ወደ ገበያው ሲገቡ በትርፋማነታቸው ላይ አሉታዊ ተጽእኖ ይኖረዋል የሚል ሰጋት አድሮባቸዋል።