"ግብረሰዶማዊነትና የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻ በህገ ተፈጥሮም ሆነ በቅዱስ መጽሃፍት የተወገዘ ነው" - አቡነ ማትያስ
የቤተክርስቲያኗ ቅዱስ ሲኖዶስ ከግንቦት 21 ጀምሮ ሲያካሂድ የቆየውን ምልዓተ ጉባኤውን አጠናቋል
በጉባኤው ውሳኔ በተደረሰባቸው ጉዳዮች ዙሪያ የቤተክርስቲያኗ ፓትሪያርክ ብጹዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ መግለጫ ሰጥተዋል
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ግብረሰዶማዊነት እና የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻን አወገዘች።
የቤተክርስቲያኗ ቅዱስ ሲኖዶስ ከግንቦት 21 ጀምሮ ሲያካሂድ የቆየውን ምልዓተ ጉባኤውን በዛሬው እለት አጠናቋል።
ቅዱስ ሲኖዶስ በምልዓተ ጉባኤው ለቤተክርስሪያኗ አንድነት፣ ለምዕመናን ደህንነት እና ሀገራዊ ሰላም ትኩረት በመስጠት መክሮ ውሳኔዎችን ማሳለፉን ነው ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ በሰጡት መግለጫ የጠቆሙት።
ቅዱስ ሲኖዶስ በሀገራዊ ወቅታዊ ሁኔታዎች እና ቤተክርስቲያኗ ከመንግስት ጋር ያላትን ግንኙነት በተመለከተ መክሮ ውሳኔዎችን ማሳለፉንም አብራርተዋል።
በመላው ሀገሪቱ በተፈጠሩ ግጭትችና አለመግባባቶች የሰዎች ህይወት መቀጠፉና የንብረት ውድመቱ መቀጠሉ ቅዱስ ሲኖዶሱን አሳዝኗል ያሉት ፓትርያርኩ፥ ሁሉም ባለድርሻዎች ከግጭትና ጥፋት ተቆጥበው ልዩነታቸውን በንግግር እንዲፈቱና ዘላቂ ሰላም እንዲረጋገጥ ጥሪ አቅርቧል ብለዋል።
የሀገራዊ ምክክር ኮሚሽኑ በሀገረ መንግስት ምስረታ፣ በሰላም ግንባታ እና አስታራቂነት ትልቅ ድርሻ ላበረከተችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የተሳትፎ ጥሪ አለማቅረቡም ቅዱስ ሲኖዶሱን ቅር እንዳሰኘ ነው ያነሱት።
ቤተክርስቲያኗ በሀገራዊ ምክክሩ የመሳተፍና አጀንዳ የማቅረብ መብቷ እንዲረጋገጥ ቅዱስ ሲኖዶሱ ከኮሚሽኑ ጋር የሚነጋገር ኮሚቴ መሰየሙንም በመጥቀስ።
ቤተክርስቲያኗ ከመንግስት ጋር መልካም ግንኙነት እንዲኖራትም ከመንግስት የስራ ሃላፊዎች ጋር የሚመክር የብጹአን ሊቃነጻጻሳት ልኡክ በቅዱስ ሲኖዶሱ መሰየሙን ገልጸዋል።
ቅዱስ ሲኖዶስ በምልዓተ ጉባኤው ከመከረባቸው ጉዳዮች መካከል የግብረሰዶማዊነት እና የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻ አንዱ ነው።
“ግብረሰዶማዊነት እና የተመሳሳይ ጾታ ጋብቻ በህገ ተፈጥሮም ሆነ በሰው ልጅ ሰብአዊ አኗኗር ፈጽሞ ተቀባይነት የሌለው፤ በቅዱሳን መጽሃፍት ፈጽሞ የተከለከለ፤ ከቤተክርስቲያን ቀኖና ውጭ የሆነና በስነልቦና ደንቦች የተወገዘ ነው” ብለዋል ፓትሪያርኩ።
ድርጊቱ “አዕምሯዊ ማንነትን የሚያዛባ፣ ግለሰባዊ ማንነትን፣ ቤተሰባዊ ህይወትን እንዲሁም ማህበራዊ ትስስርን የሚጎዳ” በመሆኑ ቅዱስ ሲኖዶሱ ያወግዘዋል ሲሉም አክለዋል።
ቤተክርስቲያኗ በተመሳሳይ ጾታ ጋብቻ እና ግብረሰዶማዊነት ዙሪያ ያላትን አቋም የሚገልጽ ዝርዝር መግለጫ በቀጣይ እንደምታወጣም ነው ፓትርያርክ አቡነ ማትያስ በመግለጫቸው ያብራሩት።
የኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያንም በታህሳስ ወር 2016 የተመሳሳይ ፆታ ጋብቻን እንደማትባርክ መግለጿ ይታወሳል።