ቤተክርስቲያኗ በግጭቶች ተሳታፊ የሆኑ ወገኖች በሰለጠነ አካሄድና በሰላማዊ መንገድ ተወያይተው እንዲፈቱ ጥሪ አቀረበች
በሀገሪቱ በተለያዩ ቦታዎች በተከሰቱ ግጭቶች ምክንያት የሰው ሕይወት እያለፈ በመሆኑ ቤተ ክርስቲያንዋ የተሰማትን ሐዘን ገልጻለች
“በኢትዮጵያ የተከሰተው የእርስ በርስ ግጭት ተወግዶ ሰላምና አንድነት እንዲሰፍን ከሁሉም በላይ እግዚአብሔርን በጾምና በጸሎት ልንማጸን ይገባል” ብላለች
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን በግጭቶች ተሳታፊ የሆኑ ወገኖች በሰለጠነ አካሄድና በሰላማዊ መንገድ ተወያይተው እንዲፈቱ ጥሪ አቀረበች።
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ሐምሌ 27 ቀን 2015 ዓ.ም ባደረገው ስብሰባ ወቅታዊ ሀገራዊ ሰላምን በተመለከተ አጀንዳ በመቅረጽ በጉዳዩ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ መግለጫ አውጥቷል።
በመግለጫውም በተለያዩ ቦታዎች እየተከሰተ ባለው የሰላም መደፍረስና የእርስ በርስ ግጭቶች ምክንያት የበርካታ ሰዎች ሕይወት እያለፈ እና በርካታ የሀገርና የሕዝብ ሀብትና ንብረት እየወደመ በመሆኑ ቤተ ክርስቲያኗ ጥልቅ ሐዘን እንደተሰማት ገልጻች።
“ሰላም ለሰው ልጆች ብቻ ሳይሆን ለሁሉም ፍጡራን መሠረታዊ ጉዳይ ነው” ያለው መግለጫው፤ በጥቅሉ ሰላም ሲጠፋ አብረው የሚጠፉ መልካም እሴቶቻችን ብዙ ናቸው ብሏል።
በኢትዮጵያ የተከሰተው የእርስ በርስ ጦርነትና ግጭት ተወግዶ ሰላምና አንድነት እንዲሰፍን ከሁሉም በላይ እግዚአብሔርን በጾምና በጸሎት ልንማጸን እንደሚገባም ቤተ ክስርቲያኗ አስገንዝባለች።
በሀገሪቱ አሁን ያለው የሰላም እጦትና የእርስ በርስ ግጭት ወደፊት ሊያስከትል የሚችለው ችግር ከፍተኛ መሆኑን በመገንዘብ ሁሉም ኢትዮጵያውያን ለአገራዊ ሰላም የበኩላቸውን ጥረት እንድታደርጉ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪ አስተላልፏል።
በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል እየተደረጉ ባሉ ግጭቶች ተሳታፊ የሆኑ ወገኖች ካለፈው የጦርነት በመማር የተፈጠረውን ችግር በጥበብና በማስተዋል እንዲሁም በሰለጠነ አካሄድና በሰላማዊ መንገድ ወያይተው እንዲፈቱ ቤተ ክርስቲያኗ የሰላም ጥሪዋ አስተላልፋለች።
የፌደራል መንግስት ባለፈው ሚያዝያ ወር በክልል ልዩ ሀይሎች ላይ የማፍረስ እና “መልሶ ማደራጀት“ ውሳኔ ካሳለፈበት ጊዜ አንስቶ በአማራ ክልል የጸጥታ ችግር እየተባባሰ መምጣ ይታወቃል።
የአማራ ክልል ርዕሰ መስተዳድር በክልሉ ያለውን ሁኔታ በመደበኛ የጸጥታ ማስከበር መቆጣጠር እንደማይቻል እና የፌደራል መንግስት ጣልቃ እንዲገባ መጠየቃቸው ይታወሳል።
ጣልቃ እንዲገባ የተጠየቀው የፌደራል በዛሬው መንግስትም በአማራ ክልል የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲታወጅ በሚኒስትሮች ምክር ቤት በኩል ወስኗል።