ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በቱርክ የሚያደርጉትን የስራ ጉብኝት ጀመሩ
ጠ/ሚ ዐቢይ በቱርክ ቆይታቸው ፕሬዚደንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶጋን ጋር ተገናኝተው በሁለትዮሽ ጉዳዮች ላይ ይመክራሉ
የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶ/ር ቀነዓ ያደታና የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዋ/ዳይሬክተር አቶ ተመስገን ጥሩነህ ከጠ/ሚሩ ጋር ወደ ቱርክ አድርገዋል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በቱርክ የሚያደርጉትን የስራ ጉብኝት ጀምረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ልዑካን ቡድናቸው በዛሬው እለት ለሥራ ጉብኝት ቱርክ፣ አንካራ ገብተዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በቆይታቸው ፕሬዚደንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶጋንን አግኝተው በሁለትዮሽ እና ቀጣናዊ የጋራ የትኩረት በሆኑ ጉዳዮች ላይ እንደሚወያዩ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ጋር ወደ ቱርክ የተጓዘው ልኡክ ውስጥ የመከላከያ ሚኒስትሩ ዶክተር ቀነዓ ያደታ፣ የብሄራዊ መረጃና ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ተመስገን ጥሩነህ እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደኤታ አቶ ሬድዋን ሁሴን ይገኙበታል።
ጠ/ሚ ዐቢይ ወደ ቱርክ ያቀኑት በፕሬዝዳንት ረሲብ ጣይብ ኤርዶጋን ግብዣ እንደሆነ የቱርክ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር መግለጫን ዋቢ አድርጎ የሃገሪቱ የዜና ወኪል አናዶሉ መዘገቡ ይታወሳል።
የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተሩ በመግለጫው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት የሃገራቱ ዲፕሎማሲያዊ የሁለትዮሽ ግንኙነት 125ኛ ዓመት ባስቆጠረበት ወቅት የሚደረግ መሆኑ ልዩ ጠቀሜታ አለው ብሏል፡፡
ጉብኝቱ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የመጀመሪያው ይፋዊ የቱርክ ጉብኝት ሲሆን፤ ሆኖም ለምን ያህል ቀናት በቱርክ ይቆያሉ ስለሚለው ነገር ከቱርክም ሆነ ከኢትዮጵያ በኩል የተገለጸ ነገር የለም።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና የቱሩክ ፕሬዚደንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶጋን ከዚህ ቀደም በስልክ መወያየታቸው ይታወሳል።
በውይይቱ ወቅትም የቱርክ ፕሬዝደንት ረሲፕ ታይፕ ኤርዶጋን ቱርክ ለኢትዮጵያ የትኛውንም አይነት ድጋፍ ታደርጋለች ማለታቸውን በፕሬዝደንቱ ይፋዊ የትዊተር ገፅ ላይ መውጣቱ ይታወሳል።
ኤርዶጋን ከጠቅላይ ሚንስትሩ ጋር በነበራቸው የስልክ ውይይት ቱርክ ለኢትዮጵያ ሰላም እና መረጋጋት ትልቅ ዋጋ ትሰጣለች ማለታቸውም ይታወሳል።