የኢትዮጵያ የማሸነፍ አቅም ተደራጅቶ እና ተጠናክሮ እየወጣ ነው- ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ
መንግስት ቃል እንደገባው እጅን በአፍ የሚያስጭን ገድል መፈጸሙ የሚበሰርበት ጊዜው ቅርብ ነው
በኢትዮጵያ ላይ የተከፈተውን የሚዲያና የዲፕሎማሲ ጫና ለመመከት ሁሉም ሀገር ወዳድ መረባረብ እንደሚገባው ጥሪ አቅርበዋል
የኢትዮጵያ የማሸነፍ አቅም ተደራጅቶ እና ተጠናክሮ እየወጣ መሆኑን የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) አስታወቁ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) ዛሬ ባወጡት መግለጫ፤ “ጠላት ወደ ወጥመድ እየገባ ነው“ ያሉ ሲሆን የማሸነፍ ዐቅም ተደራጅቶ እና ተጠናክሮ እየወጣ እንደሆነም አንስተዋል።
መንግስት ቃል የገባው “እጅን በአፍ የሚያስጭን ድል” የሚፈጸምበት እና የሚበሰርበት ጊዜው ቅርብ መሆኑን ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ አሁን ያለው ጊዜ ሴራ የሚተነተንብት እንዳልሆነ ጠቅሰዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወቅቱ፤ የኢትዮጵያን ጥቅም ለማስከበር ተገቢው ቦታ ላይ መሰለፍ የሚጠይቅበት ጊዜ እንደሆነም አንስተዋል።
የኢትዮጵያ ጠላቶች ያሏቸው ኃይሎች፤ ድሮ በድብቅ የሚያደርጉትን አሁን በግልጽ በሁለት ግንባሮች ላይ ጦርነት መክፈታቸውን ያነሱት ዶ/ር ዐቢይ፤ የጦር ግንባር እና የዲፕሎማሲ ግንባር በኢትዮጵያ ላይ መከፈታቸውንም ነው ያነሱት።
አሁን ላይ ህልውና ግድ የሚለው ሁሉ ከሴራ ትንታኔና ከአጉል መበርገግ ወጥቶ ሁለቱን ግንባሮች በይፋ እንዲቀላቀለም መንግስት ጥሪ አቅርበዋል።
መንግስት አሸባሪነት የፈረጀው “ቀሩኝ የሚላቸውን የክፋት ካርዶች ሁሉ ተጠቅሞ ሊያሸብረን፣ ሊያበጣብጠንና ሊለያየን፤ የሚችለውን ድንጋይ ፈንቅሏል“ ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ አሁን በተቃራኒው ቡድኑ “ተሳዳጅና የሞት ሽረት ሩጫ“ ውስጥ እንደሆነ አስታውቀዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፤ የምዕራቡ ዓለም ዲፕሎማሲና ሚዲያ፤ የኢትዮጵያን እጅ ለመጠምዘዝ እና የህወሃትን ድምጽ “በማስተጋባት“ ደጀን ሊሆን ጥረቱን መቀጠሉን ገልጸው፤ ኢትዮጵያውያን ከተባበሩ እና ጫናውን ለመቋቋም እንዲሁም ለመመከት ከቆረጡ ህወሃት “ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ” እንደሚያልቅለት ገልጸዋል።
ዲፕሎማሲና የውጭ ግንኙነት “ሰጥቶ በመቀበል” መርሕ የሚመራ ”የፖለቲካ ዳንስ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በትክክለኛ የግንኙነት መሥመር በተቃኘ ዲፕሎማሲ በዋናነት ተጠቃሚ የምትሆነው ኢትዮጵያ እንደሆነችም አንስተዋል።
በተቃራኒው የኢትዮጵያን ጥቅም እና ሉዓላዊነት አደጋ ላይ በሚጥል መልኩ የሚቃኝ ግንኙነት ለጊዜው ፋታ የሚሰጥ ቢመስልም ዘላቂ ጉዳቱ አመዛኝ እንደሆነ ገልጸው፤ ይኼን ለማስተከለል መንግሥት የበኩሉን እያደረገ ነው፤ ወደፊትም አቋሙን አጽንቶ እንደሚቀጥል አረጋግጠዋል።
ኢትዮጵያ፤ ዛሬም ሆነ ትናንት የውጭ ጫናዎችን “አይሆንም” ማለት ስትጀምር አፍራሽና ስም አጠልሺ የሆኑ የሚዲያና የመረጃ ዘመቻዎች እንደሚከፈቱ ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በኢትዮጵያ ላይ የተከፈተውን የሚዲያና የዲፕሎማሲ ጫና ለመመከት ሁሉም ሀገር ወዳድ ወገን መረባረብ እንደሚገባው ጥሪ አቅርበዋል።
“ተደምረን ያለንን የተጽዕኖ በር እና ዕድል ሁሉ በመጠቀም በኢትዮጵያ ላይ የተከፈተውን ዘመቻ መመከት ይገባል” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በማኅበራዊና በዋናው ሚዲያ፣ በሀገር ውስጥና በውጪ ሀገር፣ በግልና በጋራ፣ በተናጠልና በመናበብ ሀገራችንን የሚጎዱ የውሸት ዜናዎች መቃወምና ማምከን እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።