ጠ/ሚ ዐቢይ ወደ ቱርክ የሚያቀኑት በፕሬዝዳንት ረሲብ ጣይብ ኤርዶጋን ግብዣ ነው
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ (ዶ/ር) ነገ ረቡዕ ነሃሴ 12 ቀን 2013 ዓ/ም ለይፋዊ ጉብኝት ወደ ቱርክ እንደሚያቀኑ ተሰማ፡፡
ጠ/ሚ ዐቢይ ወደ ቱርክ የሚያቀኑት በፕሬዝዳንት ረሲብ ጣይብ ኤርዶጋን ግብዣ እንደሆነ የቱርክ የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር መግለጫን ዋቢ አድርጎ የሃገሪቱ የዜና ወኪል አናዶሉ ዘግቧል፡፡
የኮሙኒኬሽን ዳይሬክተሩ በመግለጫው የጠቅላይ ሚኒስትሩ ጉብኝት የሃገራቱ ዲፕሎማሲያዊ የሁለትዮሽ ግንኙነት 125ኛ ዓመት ባስቆጠረበት ወቅት የሚደረግ መሆኑ ልዩ ጠቀሜታ አለው ብሏል፡፡
በጉብኝቱ በሁለትዮሽና በሌሎችም ወቅታዊ ሃገራዊ እና ቀጣናዊ ጉዳዮች ላይ ውይይት እንደሚደረግም በመግለጫው ተጠቅሷል፡፡
ጉብኝቱ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የመጀመሪያው ይፋዊ የቱርክ ጉብኝት ነው የሚሆነው፡፡
ሆኖም ለምን ያህል ቀናት በቱርክ ይቆያሉ ስለሚለው ነገር ከቱርክም ሆነ ከኢትዮጵያ በኩል የተገለጸ ነገር የለም፡፡
የሱዳን ሉዓላዊ የሽግግር ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ሌ/ጄ አል ቡርሃን ከሰሞኑ በቱርክ ጉብኝት ማድረጋቸውም አይዘነጋም፡፡
ቱርክ ከሰሞኑ የትኛውንም ዐይነት ድጋፍ ለኢትዮጵያ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን ገለጸች መባሉ የሚታወስ ነው፡፡