በኢትዮጵያ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ84 ቀናት በኋላ ከፍተኛ ሆኖ መመዝገቡ ተገለጸ
በኢትዮጵያ ያለው የኮቪድ-19 ስርጭት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱን የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገልጿል
በበሽታው የሚያዙ፣ በጽኑ የሚታመሙና ህይወታቸውን የሚያጡ ሰዎች ቁጥር በከፍተኛ መጠን መጨመሩንም አስታውቋል
በኢትዮጵያ በኮቪድ-19 የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከ84 ቀናት በኋላ ከፍተኛው ሆኖ መመዝገቡን የኢትዮጵያ የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
በኢትዮጵያ ያለው የኮቪድ-19 ስርጭት አሳሳቢ ደረጃ ላይ መድረሱንም አል ዐይን ኢንስቲትዩቱ ያገኘው መረጃ ያመለክታል።
ይህም በበሽታው የሚያዙ፣ በጽኑ የሚታመሙና ህይወታቸውን የሚያጡ ወገኖቻችን ቁጥር ከሌላው ጊዜ በተለየ ሁኔታ በከፍተኛ መጠን መጨመሩን ያመላክታለ ብሏል።
ባሳለፍነው ሀሙስ ዕለት ለ7 ሺህ 598 የላብራቶሪ ምርመራ የተደረገ ሲሆን 687 ግለሰቦች በኮቪድ-19 መያዛቸው ተረጋግጧል።
ይህ ማለት ናሙና ከሰጡ 100 ግለሰቦች ዘጠኙ ማለትም 9 በመቶው የኮቪድ-19 ቫይረስ ተገኝቶባቸዋል፤ 270 ግለሰቦች ደግሞ በፅኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ ይገኛሉ።
በትናትናው እለት ይሃ በተደረገው ሪፖርትም ለ7 ሺህ 983 ሰዎች የላቦራቶሪ ምረመራ ተደርጎ 854 ሰዎች ላይ ቫይረሱ መገኘቱን ተመላቷል።
276 ግለሰቦች ደግሞ በፅኑ ህሙማን ክፍል ውስጥ የሚገኙ ሲሆን፤ የ9 ሰዎች ህይወት ማለፉም በሪፖርቱ ተገልጿል።
በኮቪድ-19 የሚያዙ ሰዎች ቁጥር በዚህ ፍጥነት እጨመረ የሚሄድ ከሆነ ወደ ፅኑ ህሙማን ክፍል የሚገቡ ሰዎች ቁጥር ይጨምራል ብሏል ኢንስቲትዩቱ።
ይህ ደግሞ በኮቪድ-19 ህክምና ማዕከላት ላይ ከፍተኛ የሆነ የአልጋ፣ ሰው ሰራሽ የመተንፈሻ መሳሪያ እና ኦክስጂን እጥረት ሊያስከትል ይችላልም ብሏል።
በኮቪድ-19 ቫይረስ የሚያዙ ወደ ፅኑ ህሙማን ክፍል የሚገቡ እና ህይወታቸውን የሚያጡ ግለሰቦች ቁጥር እያሻቀበ መሆኑንም አስታውቋል።
ስለሆነም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ማስክ በማድረግ፣ የእጅን ንጽህና በተደጋጋሚ በመጠበቅ፣ በየትኛውም ቦታ አካላዊ ርቀትን በመጠበቅ በተጨማሪም የኮቪድ-19 ክትባት በመከተብ የኮቪድ-19 ወረርሽኝ የከፋ ችግር እንዳያስከትል በጋራ የኮቪድ-19 መከላከያ መንገዶች ተግባራዊ እንዲያደርጉ ኢንስቲትዩቱ ጥሪ አቅርቧል።