በኢትዮጵያ ከ430 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎች የኮቪድ-19 ክትባትን ተከትበዋል- ጤና ሚኒስቴር
በቅርቡ ከ5 ሚሊየን በላይ ክትባት ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት እየተሰራ ነው
ከክትባቱ ጋር ተያይዞ ከሌሎች ክትባቶች በተለየ መልኩ የደረሰ ከፍተኛ ጉዳት አለመኖሩን ዶ/ር ሊያ ገልጸዋል
በኢትዮጵያ እስካሁን ከ430 ሺህ በላይ የሚሆኑ ሰዎች የኮቪድ 19 መከላከያ ክትባት መከተባቸውን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ።
የጤና ሚኒስትር ዶ/ር ሊያ ታደሰ ዛሬ በሰጡት መግለጫ ፣ ክትባቱ መሰጠት ከጀመረበት ከመጋቢት 4 አንስቶ እስካሁን ከ430 ሺህ በላይ የሚሆኑ የሚመለከታቸው የህብረተሰብ ክፍሎች መከተባቸውን አስታውቀዋል።
በዚህ ሂደትም ከክትባቱ ጋር ተያይዞ ከሌሎች ክትባቶች በተለየ መልኩ የደረሰ ከፍተኛ ጉዳት አለመኖሩን በመግለጽ፤ የሚወጡ መረጃዎችን እና በኢትዮጵያ ያለውን ሁኔታ በየጊዜው የሚገመግም ብሄራዊ ግብረ ኃይል እየሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።
ቀሪውን ክትባት በተፋጠነ ሂደት ለማዳረስ እየተሰራ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትሯ፤ በቅርቡ ከ5 ሚሊየን በላይ ክትባት ወደ ሀገር ውስጥ ለማስገባት እየተሰራ መሆኑንም አንስተዋል።
ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የቫይረሱ ስርጭት በከፍተኛ ደረጃ እየጨመረ መሆኑን ያነሱት ዶ/ር ሊያ፤ ይህንን ተከትሎ በመከላከያ መንገዶቹ ተግባራዊነት ላይ ክትትል ማድረግ ተጀምሯል ብለዋል።
በተደረገው ቁጥጥርም ከ73 ሺህ የሚበልጡ ግለሰቦች ማስክ ባለማድረግ እና አካላዊ ርቀት ባለመጠብቅ በፖሊሶች ተይዘው የተለያዩ የማስተማሪያ እርምጃዎች እንደተወሰዱባቸው ነው የገለጹት፡፡ ደንቦቹን የተላለፉ 400 በላይ ድርጅቶች ህጋዊ ማስጠንቀቂያ ሲሰጣቸው 30 ግለሰቦችና 16 ተቋማት ጉዳያችው በህግ በመታየት ላይ መሆንንም አስታውቀዋል።
የጤና ተቋማትን አቅም ለማሳድግ ፣ እለታዊ የኦክስጂን አቅርቦትን በ2,500 ሲሊንደር ከፍ ማድረግ እና አቅርቦቱን ከ 4,000 ሲሊንደር ወደ 6,500 ማሳድግ ተችሏል ብለዋል።
215 ተጨማሪ የመተንፈሻ ማሽኖች ለተቋማት እየተሰራጩ መሆኑን በመጥቀስ ይህም ለኮቪድ-19 ህክምና የሚውሉ የማሽኖች ቁጥር ከ258 ወደ 473 የሚያሳድግ መሆኑንና የኮቪድ ጽኑ ህክምና አቅምን ደግሞ ከ652 ወደ 892 ከፍ እንደሚያደርግ አስታውቀዋል።
በኢትዮጵያ የኮቪድ 19 ስርጭት ምጣኔ
እስካለፈው ቅዳሜ በነበሩት 10 ቀኖች ውስጥ፣ ከ 20 ሺህ 600 በላይ ሰዎች፣ ቫይረሱ ተገኝቶባቸዋል፤ ከወር በፊት በነበሩት 10 ቀናት፣ በቫይረሱ ተይዞ ከነበረው (10,800) ሰውጋርሲነጻጸር፣ የ91 ከመቶ ጭማሪ አሳይቷል።
እስከ ትናንት እስከ ሚያዝያ 7 ድረስ የጽኑ ህክምና የሚፈልጉ ህሙማን 1031 መድረሱንም በመግለጫው አመላክተዋል።
በህክምና ተቋማት ውስጥ እስካለፈው ቅዳሜ በነበሩት 10 ቀኖች ውስጥ ብቻ 275 ሰዎች በበሽታው የሞቱ ሲሆን፤ በአማካይ በየቀኑ የ28 ሰዎችን እያለፈ ነውም ብለዋል።
የአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ በመቃብር ቦታዎች ባጠናው ጥናት ፣ በመጋቢት ወር የሞት መጠን ከአምናው ተመሳሳይ ወር ጋር ሲነጻጸር የ37 በመቶ ጭማሪ እንዳለው እንደሚያሳይም ገልጸዋል።