“ያደጉ ሃገራት ያጋበሱት ክትባት ዝቅተኛ ገቢ ወዳላቸው ሃገራት በአስቸኳይ እንዲመለስ እንፈልጋለን”- ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም
ፈረንሳይና ጀርመንን ይህን የዓለም ጤና ድርጅትን ጥሪ ችላ በማለት ለዜጎቻቸው 3ኛ ዙር ክትባቶችን ለመስጠት ተዘጋጅተዋል
ዶ/ር ቴድሮስ ብዙዎች አንደኛ ዙር የኮሮና ክትባቶችን ባላገኙበት ያደጉት ሃገራት 3ኛ ዙር ለመከተብ ማሰባቸውን የዓለም ጤና ድርጅት ተቃውመዋል
አንደኛ ዙር የኮሮና ቫይረስ ክትባቶችን ያላገኙ በርካታ የዓለማችን ሃገራት እያሉ ያደጉት ሃገራት 3ኛ ዙር ለመከተብ ማሰባቸውን የዓለም ጤና ድርጅት ተቃወመ፡፡
የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ቴድሮስ አድሃኖም የዓለምን አብላጫ የክትባት አቅርቦት የተጠቀሙት ያደጉት ሃገራት ይህን ለማድረግ መዘጋጀታቸውን አንቀበልም ብለዋል፡፡
አብላጫው የዓለም ህዝብ ለወረርሽኙ አሁንም ተጋላጭ ሆኖ ባለበት ሁኔታ ይህን ማድረጉ ተገቢ እንዳይደለም ነው ዶ/ር ቴድሮስ የገለጹት፡፡
ከፍተኛ ገቢ ወዳላቸው ያደጉ ሃገራት የሄዱ ክትባቶች አጥብቀው ወደሚፈልጓቸውና ዝቅተኛ ገቢ ወዳላቸው ሃገራት በአስቸኳይ እንዲመለሱ እንሻለንም ብለዋል፡፡
ሆኖም ፈረንሳይና ጀርመንን መሰል የአውሮፓ ሃገራት ይህን የዓለም ጤና ድርጅትን ጥሪ ችላ በማለት አሁንም ተጋላጭ ናቸው ላሏቸው ዜጎቻቸው ሶስተኛ ዙር ክትባቶችን ለመስጠት ተዘጋጅተዋል፡፡
ከመጪው መስከረም ጀምሮ ክትባቱን መስጠት እንደሚጀምሩም ነው ፍራንስ 24 የዘገበው፡፡
ዓለም በአሁኑ ወቅት ከጀርመን፣ ፈረንሳይና ስፔን አጠቃላይ ህዝብ ቁጥር የበለጠ የቫይረሱ ተጠቂ ቁጥር አላት፡፡
የ4 ነጥብ 25 ሚሊዬን ሰዎች ህይወትም አልፏል፡፡
ይህ ሆኖ ባለበት ሁኔታ ነው ኢ- ፍትሐዊ የክትባቶች ተደራሽነት እና ያደጉት ሃገራት ክትባቶችን የማጋበስ አባዜ ዓለምን እየፈተነ ያለው፡፡
በወረርሽኙ የላሸቀው የዓለም ምጣኔ ሃብት በቶሎ እንዳያገግምም ምክንያት ሆኗል እንደ ዓለም ጤና ድርጅት ገለጻ፡፡
ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው ሀገሮች ከፍተኛ ገቢ ካላቸው አገሮች ጋር ተመሳሳይ የክትባት መጠን ቢኖራቸው በተያዘው ዓመት ጠቅላላ የሀገር ውስጥ ምርታቸው (ጂዲፒ) ላይ 38 ቢሊዮን ዶላር ሊጨምሩ እንደነበርም ድርጅቱ አመልክቷል ።