ኢትዮጵያ በተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ይሰየማል የተባለውን መርማሪ ቡድን እንደማትቀበል አስታወቀች
ሚኒስቴሩ የፖለቲካ መጠቀሚያ ሆኗል ባለው በምክር ቤቱ ድርጊት ማዘኑንም ነው የገለጸው
ቡድኑ ከስምምነት ውጭ የሚቋቋም ነው ያለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከቡድኑ ጋር እንደማይተባበር አስታውቋል
ኢትዮጵያ በተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ይሰየማል የተባለውን መርማሪ ቡድን እንደማትቀበል አስታወቀች፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በዛሬው የምክር ቤቱ ልዩ ስብበሳ አዲስ የመብት ጥሰት ምርመራ እንዲካሄድ የቀረበው ሃሳብ በአብላጫ ድምጽ መጽደቁን በማስመልከት የተቃውሞ መግለጫ አውጥቷል፡፡
በመግለጫው የሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽኑ አሁንም ለአንዳንዶች ፖለቲካ መጠቀሚያ ሆኖ በመገኘቱ ማዘኑን የገለጸው ሚኒስቴሩ ምክር ቤቱ ልዩ ስብሰባው እንዳይካሄድ ደጋግሞ ከጠየቀው የጉዳዩ ባለቤት ሃገር ጋር ባለመነጋገሩና ባለመተባበሩ ምክንያት አንዳንዶች አብላጫ ድምጽ በማግኘት ዓላማቸውን ከግብ ለማድረስ ተሳክቶላቸዋል ብሏል፡፡
አዲስ የሰብዓዊ መብቶች ጥሰት ምርመራ እንዲካሄድ የቀረበው የውሳኔ ሃሳብ በዛሬው የምክር ቤቱ ልዩ ስብሰባ መጽደቁን አስመልክቶ ባወጣው መግለጫ፡፡
ይህ ኮሚሽኑ ከኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጋር በመጣመር ባደረገው ምርመራ የተሰጡ ምክረ ሃሳቦችን በመተው የሆነ ነውም ብሏል፤ ኢሰመኮ ለምክረ ሃሳቦቹ ተግባራዊነት ሁሉም የምክር ቤቱ አባላት ድጋፋቸውን እንዲሰጡ ከሶስት ቀናት በፊት ባሳለፍነው ማክሰኞ ታህሳስ 5 ቀን 2014 ዓ/ም ለምክር ቤቱ ፕሬዝዳንት ጥያቄ ማቅረቡን በማስታወስ፡፡
ኢሰመኮ ይደገፍ ሲል የጠየቀለት ምክረ ሃሳብ የተቋቋመው የሚኒስትሮች ግብረ ኃይል እና ከተመድ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጋር በመተባበር የተጀመረው ጣምራ ምርመራ ይቀጥል የሚል ነበር፡፡
በአንዳንድ የምክር ቤቱ አባላት በሉዓላዊት ሃገር የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መገቢያ መንገዶችን ለመፈለግ የተደረገው ጥረት ሁኔታውን ከማባባስ ውጭ ሊፈይድ የሚችለው ነገር እንደሌለም በመግለጫው አስቀምጧል፡፡
በምክር ቤቱ በኩል እንዲህ ዐይነት መንገዶችን ለማመቻቸት ከተደረጉ ጥረቶች ብዙዎቹ ሳይሳኩ መቅረታቸውን ያስታወሰው ሚኒስቴሩ ጣልቃ ገብነትን በማይፈቅዱ ሃገራት ላይ ጫና ማድረጊያ መንገድ ነውም ብሏል፡፡
ኢትዮጵያ የምክር ቤቱን ተዓማኒነት ከምንም በላይ ደግሞ የኢትዮጵያን ግዛታዊ አንድነት፣ ሉዓላዊነት እና ፖለቲካዊ ነጻነት በሚያሳጣው በእንዲህ ዐይነቱ ፖለቲካ የተጫነው ውሳኔ ምክንያት የልዩ ስብሰባውን መካሄድ አጥብቃ መቃወሟንም ገልጿል፡፡
ከስምምነት ውጭ ከሚቋቋመው መርማሪ አካል ጋር እንደማትተባበርም ነው ሚኒስቴሩ ያስታወቀው፡፡
ኢትዮጵያን የደገፉ ሃገራትን ያመሰገነም ሲሆን ለሰብዓዊ መብቶች መከበርና መጠበቅ በዓለም አቀፍ ህግጋት መሰረት ግዴታዎቹን መወጣቱን እንደሚቀጥል አስታውቋል፡፡
አስገዳጅ የተናጠል እርምጃዎች እና በሰብዓዊ መብቶች ሰበብ በሃገራት የውስጥ ጉዳይ ጣልቃ መግባቱ ይብቃ ብሏልም ሚኒስቴሩ በመግለጫው፡፡
በአውሮፓ ህብረት ጠያቂነት ዛሬ አርብ ታህሳስ 8 ቀን 2014 ዓ/ም በተካሄደው የተመድ ሰብዓዊ ምክር ቤት ልዩ ስብሰባ አዲስ ምርመራ እንዲደረግና መርማሪ አካል እንዲሰየም የቀረበው የውሳኔ ሃሳብ
በ21 የድጋፍ፣በ15 የተቃውሞ እና በ11የተዓቅቦ ድምጾች መጽደቁ ይታወሳል።
በውሳኔው መሰረት በተመድ ሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ሶስት መርማሪ ባለሙያዎች ይሰየማሉ፡፡
ምርመራው በተመድ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንና በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጥምረት ለአንድ ዓመት የሚካሄድ ሲሆን እንደየሁኔታው ሊራዘም ይችላል፡፡