ኢትዮጵያ የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አባል ሃገራት ለመጪው አርብ የተቀጠረውን ስብሰባ ውድቅ እንዲያደርጉ ጠየቀች
ምክር ቤቱ በዚህ ወቅት ይህን ከማሰብ ይልቅ በህወሓት ኃይሎች የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን መመርመር ላይ ሊጠመድ ይገባ ነበርም ነው ኢትዮጵያ በመግለጫዋ ያለችው
የምክር ቤቱ አካሄድ የተደረጉ ጥረቶችን ያላገናዘበ ነው ያለችው ኢትዮጵያ ከበስተኋላው የፖለቲካ ዓላማን ያነገበ ነውም ብላለች
ኢትዮጵያ፤ የተባበሩት መንግስታት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አባል ሃገራት ለመጪው አርብ የተቀጠረውን የምክር ቤቱን የጄኔቭ ስብሰባ ውድቅ እንዲያደርጉ ጠየቀች፡፡
አባል ሃገራቱ ፖለቲካ በተጫነው በልዩ ስብሰባው ላይ የተቃውሞ ድምጽን እንዲሰጡም ጥሪ አቅርባለች፡፡
በሁኔታው ማዘኗን በመግለጽ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሯ በኩል ባወጣችው መግለጫ፤ ከዚህ በፊት በመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አማካይነት የተካሄደውን ምርመራ መሠረት በማድረግ እርምጃ እየወሰደች ባለበት ጊዜ ልዩ ስብሰባ መጥራት የሚያሳዝን እና "ፖለቲካዊ ፍላጎት" ያለው ስትል ተቃውማለች።
የተጠራው የሰብዓዊ መብት ምክር ቤቱ አባላት ልዩ ስብሰባ "ፖለቲካዊ አላማን ያነገበ ነው"ም ነው ኢትዮጵያ ያለችው፡፡
የፊታችን አርብ በጀኔቫ ይካሄዳል የተባለለትን ልዩ ስብሰባ በአውሮፓ ህብረት ጠያቂነት የሚካሄድ ሲሆን ከምክር ቤቱ 47 አባላትና ታዛቢዎች መካከል ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ በአንድ ሦስተኛው አባል ሀገራት ደግፈውታል፡፡
በስብሰባው በጦርነቱ ተሳታፊ በሆኑ በሁሉም ወገኖች የተፈጸሙ የመብት ጥሰቶችን የሚያወግዝ የውሳኔ ሐሳብ እንደሚቀርብ የተገለጸም ሲሆን ተቀባይነት ካገኘ በኢትዮጵያ ተጨማሪ ምርመራ የሚያደርግ ዓለም አቀፍ የሰብዓዊ መብቶች ባለሙያዎች ኮሚሽን እንዲቋቋም ይደረጋል እንደ ሮይተርስ ዘገባ፡፡
ተፈጽመዋል የተባሉ የመብት ጥሰቶችን በጋራ ለመመርመር ብዙ ጥረት ከተደረገና ውጤቱም ከወር በፊት ይፋ ከሆነ በኋላ ይህ መሆኑ አግባብነት እንደሌለው በማስታወቅ የተቃውሞ መግለጫን ያወጣችው ኢትዮጵያም ልክ ከአሁን ቀደም ሲደረግ እንደነበረው ሁሉ ጫናዎችን ለማድረግ ነው በሚል ስብሰባው ውድቅ እንዲደረግ ጠይቃለች፡፡
የትግራይ ግጭት ተሳታፊዎች “በተለያየ መጠን” የሰብአዊ መብቶችን መጣሳቸውን የምርመራ ቡድኑ ገለፀ
ምክር ቤቱ በአሁኑ ወቅት ቅድሚያ ሊሰጥ ይገባ የነበረው “በአፋር እና በአማራ ክልሎች በህወሓት ኃይሎች የተፈጸሙትንና እየተፈጸሙ ያሉትን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና ጭፍጨፋዎችን መመርመር ላይ” ነበርም ብላለች በመግለጫው፡፡
ጣምራ የምርመራ ሪፖርቱ ይፋ በሆነበት ጊዜ የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ሚሼል ባችሌት ጦርነቱን ተከትሎ የተፈጸሙት የመብት ጥሰቶች “የጦር ወንጀል” ሊሆኑ እንደሚችሉ መናገራቸው ይታወሳል።
የህወሓት ታጣቂዎች በንፋስ መውጫ ከተማ በ9 ቀናት ውስጥ 71 ሴቶችን አስገድደው ደፍረዋል - አምነስቲ
ከአንድ ዓመት በፊት ትግራይ ውስጥ ተጀምሮ በአሁኑ ጊዜ አማራ እና አፋር ክልሎችን ባዳረሰው የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ለሞት እንዲሁም ሚሊዮኖች ደግሞ ለመፈናቀል መዳረጋቸውን መረጃዎች ይጠቁማሉ፡፡