በኢትዮጵያ አዲስ የመብት ጥሰት ምርመራ እንዲካሄድ የቀረበው ሃሳብ ጸደቀ
በውሳኔው መሰረት በተመድ ሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ሶስት መርማሪ ባለሙያዎች ይሰየማሉ ተብሏል
ሃሳቡ በ21 ድጋፍ እና በ15 ተቃውሞ የጸደቀ ሲሆን ሱዳንን ጨምሮ 11 ሃገራት ድምጽ ከመስጠት ታቅበዋል
በኢትዮጵያ ተፈጽመዋል የተባሉ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን የሚመረምር ገለልተኛ አካል ይቋቋም በሚል ለተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት የቀረበው ሃሳብ ጸደቀ፡፡
በአውሮፓ ህብረት ጠያቂነት የቀረበውን ሃሳብ በማስመልከት ምክር ቤቱ ዛሬ ልዩ ስብሰባ አካሂዷል፡፡
በስብሰባው ቀደም ሲልም ሃሳቡን በመቃወም አባል ሀገራቱ ውድቅ እንዲያደርጉት ጠይቃ የነበረችው ኢትዮጵያ ከአሁን ቀደም የተመረመረውን ጉዳይ ዳግም የሚመረምር አካል ይቋቋም መባሉ ላይ ያላትን ተቃውሞ አቅርባለች፡፡
ምክር ቤቱ ማየት የሌለበትን ፖለቲካዊ ጉዳይ እየተመለከተ እንደሆነ በማስታወቅም ጉዳዩን በማስመልከት የተሰጠው የውሳኔ ሃሳብ እንዲሰረዝም ጠይቃ ነበር በጄኔቭ ቋሚ ተወካይዋ አምባሳደር ዘነበ ከበደ በኩል፡፡
ሃገራትም የቀረበው ሃሳብ ተገቢነት አለው የለውም፣ የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ይጋፋል አይጋፋም በሚል ሲደግፉና ሲቃወሙ ነበር በስብሰባው፡፡
ሆኖም ከ47ቱ የምክር ቤቱ ሃገራት 21ዱ ሃሳቡን መደገፋቸውን፣15 መቃወማቸውንና ቀሪ 11 ሃገራት ደግሞ ድምጽ ከመስጠት መቆጠባቸውን ከምክር ቤቱ የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
በውሳኔው መሰረት በተመድ ሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ሶስት መርማሪ ባለሙያዎች ይሰየማሉ፡፡
ምርመራው በተመድ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽንና በኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ጥምረት ለአንድ ዓመት የሚካሄድ ሲሆን እንደየሁኔታው ሊራዘም ይችላል፡፡