ከጤናው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መመሪያዎች ውስጥ የትኞቹ ተሻሻሉ?
በኢትዮጵያ አስገዳጅ የለይቶ ማቆያ ጊዜ 14 ቀን ወደ 7 ቀን ዝቅ ማለቱን ጤና ሚኒስቴር አስታወቀ
ኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ካወጣቻቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መመሪያዎች ውስጥ የተወሰኑት ተሻሻሉ
ኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል ካወጣቻቸው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መመሪያዎች ውስጥ የተወሰኑት ተሻሻሉ
የኢትዮጵያ የጤና ሚኒስቴር የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመከላከል በወጣው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ስር ባሉ መመሪያዎች ላይ ማሻሻያዎች እንደተደረገባቸው አስታውቋል፡፡
በአዋጁ መሰረት ከውጭ የሚገቡ ሰዎች ለ14 ቀናት በለይቶ ማቆያ አንዲቆዩ የሚያስገድደው መመሪያ ተሻሽሎ ወደ 7 ቀን ዝቅ ማለቱን ሚኒስቴሩ አስታውቋል፡፡
ሚኒስቴሩ እንደገለጸው ከውጭ የሚመጡ ሰዎች ኢትዮጵያ ውስጥ ከመግባታቸው በፊት ባሉት ሶስት ቀናት ውስጥ ከቫይረሱ ነጻ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ መረጃ ካቀረቡ ናሙና ተወስዶ በቤታቸው ለ14 ቀናት ክትትል ይደረግባቸዋል፡፡
የአስከሬን ምርመራ ውጤት ከመምጣቱ በፊት ቀብር ማስፈጸም አይቻልም የሚለው የአዋጁ መመሪያም ተሻሽሎ የምርመራ ውጤት ሳይመጣ መቅበር እንደሚቻል ሚኒስቴሩ ገልጿል፡፡
“በማሻሻያው መሠረት በተለያዩ ምክንያቶች ለሞት የሚዳረጉ ዜጎች አስፈላጊውን ጥንቃቄ በማድረግ በማኅበረሰቡ የቀብር ሥነ-ሥርዓት መፈጸም ተፈቅዷል”ብሏል ሚኒስቴሩ።
ነገርግን እንደሚኒስቴሩ ገለጻ በአዋጁ ላይ 50ሰዎች ብቻ ተገኝተው ቀብር ማድረግ አለባቸው የሚለው መመሪያ አልተሻሻለም ብሏል፡፡
ዓለምአቀፍ ወረርሽኝ የሆነው ኮሮና ቫይረስ ኢትዮጵያ ውስጥ መግባቱ ከተረጋገጠበት መጋቢት 4፣ 2012 ዓ.ም በኋላ የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል መንግስት የየብስ ድንበርን ከመዝጋት በረራን እስከማቋረጥ፤ ትምህርት ቤት ከመዝጋት ፍርድቤት እስከመዝጋት የደረሰ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
ስርጭቱን ለመግታት ተጨማሪ ርምጃዎች ያስፈልጉኛል ያለው መንግስት እስከ ነሀሴ ወር ድረስ የሚቆይ የአምስት ወር የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ አውጇል፡፡ አዋጁ ማስክ ማድረግን፣ከአራት ሰዎች በላይ የሚደረግ ስብሰባን መከልከልንና የተለያዩ የትራንስፖርት መመሪያዎች ወጥቷል፡፡
በኢትዮጵያ እስከሁን ኮሮና ቫይረስ ለ72 ሰዎች ሞት ምክንያት ሲሆን 4070 ሰዎችን ደግሞ አጥቅቷል፡፡ በቫይረሱ ከተያዙት መካከል እስካሁን 1027 ሰዎቸ ደግሞ ከቫይረሱ ማገገም ችለዋል፡፡