የዓለም ከተማ ጤና ባለሙያዎች ገበያተኛውን ለምን ተበርክከው ተማጸኑ?
“ትጠቅማለችሁ ብሎ የሚሰማን ሰው ካለ ሰይጣን ራሱ ኮሮናን ለመከላከል መጣሁ ቢለን አብረነው እንሰራለን ብለን ነው የተነሳነው”
“ምን ያህል እንደተቸገርን ማህበረሰቡ እንዲያውቅልን በሚል አድርገነዋል” -ዶ/ር በላይ ገለታ፣ የእናት ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር
የዓለም ከተማ ጤና ባለሙያዎች ገበያተኛውን ለምን ተበርክከው ተማጸኑ?
ዛሬ በማህበረሰብ የትስስር ገጾች ጎልተው ሲንሸራሸሩ ከዋሉ አንኳር ጉዳዮች መካከል አንዱ በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን የመርሃቤቴ ወረዳ ጤና ባለሙያዎች ያደረጉት ሰናይ ተግባር ነው፡፡
በከተማዋ ከሚገኘው እናት ሆስፒታል፣ከከተማው እና ከወረዳው ጤና ጽህፈት ቤቶች የተውጣጡት ባለሙያዎቹ ወደ ከተማው የገበያ ስፋራ በመውጣት ተንበርክከው ማህበረሰቡ ራሱን ከአስከፊው የኮሮና ወረርሽኝ እንዲጠብቅ ተማጽነዋል፡፡
ይህን ያደረጉት የህክምና ጋውናቸውን በመልበስ ነው፡፡ ቁጥራቸውም ከ20 እስከ 30 ይደርሳል፡፡
ባለሙያዎቹ ምን ቢያሳስባቸው ነው ይህን ያደረጉት?
አል ዐይን አማርኛ ይህን ጥያቄ ለመመለስ የሚያስችሉ ጥረቶችን አድርጓል፡፡ የእናት ሆስፒታል ሜዲካል ዳይሬክተር ዶ/ር በላይ ገለታን ጨምሮ ሌሎች የሆስፒታሉንና የከተማውን አስተዳደር አካላትንም ጠይቋል፡፡
ከእለት ወደ እለት እየከፋ የመጣውን ወረርሽኙን እንዴት ልንገታው እንደምንችል የሚያሳውቁ ብዙ ነገሮች በእጅ ስልካችን ሳይቀር አሉ የሚሉት ሜዲካል ዳይሬክተሩ ዶ/ር በላይ “ሁልጊዜም የሚነገሩትን የጥንቃቄ መንገዶች በሆስፒታላችን ጭምር ለመተግበር ጥረት ብናደርግ፤ ለማስተማር ብንሞክርም ወደ ማህበረሰቡ ወረድ ብለን ስናይ ግን ግንዛቤው በተጨባጭ እንዳልደረሰ እና ሊያስተማምን የሚችል የባህሪ ለውጥ እንዳልመጣ እናያለን” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
ዶ/ር በላይ “ከጥንቃቄ መንገዶቹ አንዱ የሆነው መታጠብ ሲተገብር ብናስተውልም እንኳን አካላዊ ርቀትን ከመጠበቅ አንጻር በተለይም ዛሬን በመሳሰሉ የገበያ ቀኖች ላይ በጣም ከቁጥጥር ውጭ የሆኑ ችግሮች እንዳሉ እንመለከታለን” ሲሉም ነው የሚናገሩት፡፡
“ማህበረሰቡ ይሰማል፤ያውቃል ግን ያን ያህል አይደለም ስለዚህ እኛ ምን ያህል እንደተቸገርን ያለውን ነገር እንዲያውቅ በተግባር ሄደን እንድንናገር ብለን ነው” በገበያ ስፍራው ተገኝተን ተንበርክከን የተማጸንነው ሲሉም ያስቀምጣሉ፡፡
እኛም ጋር የማይቀር ጉዳይ ስለሆነ ቢያንስ የምንችለውን ያህል የተወሰነ እናድርግ በሚል ምክንያት እንዳደረጉትም ነግረውናል፡፡
የማህበረሰቡ አጸፋ ምን ይመስል ነበር?
ብዙዎች ‘ልብ የሚነካ’ ባሉት በዚህ ተግባር መገረማቸውን እና ማዘናቸውን ገልጸዋል፡፡ የባለሙያዎቹን ሃሳብ በመተግበር ‘ራሳችንን እንጠብቅ ለባለሙያዎቹም እናስብላቸው’ ሲሉም አጸፋዊ ምላሽን ሰጥተዋል፡፡
ባለሙያዎቹ ጋውን ለብሰው ተንበርክከው ማህበረሰቡን ራሱን እንዲጠብቅ ሲያስተምሩ እና ሲማጸኑ የተመለከተው ህዝብ እንዲሁ ዓይነት የማዘንና የመገረም አጸፋዎችን ይሰጥ እንደነበርም “ማስክ አርገን ጋውን ለብሰን ነው የወጣነው” የሚሉት ዶ/ር በላይ ለአል ዐይን ገልጸዋል፡፡
“ማህበረሰቡ በተለይም ከአካባቢው ገጠራማ ስፍራዎች የመጡት ግርምትን አጭሮባቸዋል ደንግጠው የሚያዩንም ነበሩ፤ የከተማው ሁል ጊዜ ስለሚነገረው ማስክ እያደረገ ነው ገጠር ቀበሌዎች ላይ ግን ችግር አለ ቢሆንም የለበሰውን ሸፈን አድርጎ ሲከታተለን እንደነበርም ተመልክተናል” ሲሉም ነው ዶ/ር በላይ የሚያክሉት፡፡
የማህበረሰቡ አቀባበል ጥሩ እንደነበር የገለጹም ሲሆን ወደፊት ህዝብ ሊሰባሰብ በሚችልባቸው አጋጣሚዎች ሁሉ ሁኔታዎችን እያመቻቹ ማስተማሩን ለመቀጠል እንደሚያስቡም ተናግረዋል፡፡
ዶ/ር በላይ “የምንጠቅም ከሆነና ትጠቅማለችሁ ብሎ የሚሰማን ሰው ካለ ሰይጣን ራሱ ኮሮናን ለመከላከል መጣሁ ቢለን እንኳን አብረነው እንሰራለን ብለን ነው የተነሳነው” ሲሉ ከማንም ጋር ቢሆን ተባብሮ ለመስራት ያላቸውን ዝግጁነት ገልጸዋል፡፡
ማህበረሰቡ በባለሙያዎቹ ተግባር ልቡ እንደተነካ እኛም ተመልክተናል የሚሉት የሆስፒታሉ ስራ አስኪያጅ አቶ አለባቸው አቢወይ በበኩላቸው “የማህበረሰቡን መለወጥ በተግባር ነው ልናረጋግጥ የምንችለው ለዚህም የባህሪ ለውጥ አምጥቶ ልንመለከተው ይገባል” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የባለሙዎቹ የሌላውም አካል ልፋት ውጤታማነት በዚሁ ሊረጋገጥ እንደሚገባውም ነው ስራ አስኪያጁ የተናገሩት፡፡
የከተማው አስተዳደር ለማህበረሰቡ ከወረርሽኙ መጠበቅ ከሆስፒታሉ እና በወረዳው ከሚገኙ ሌሎች የጤና ተቋማት ጋር ተቀናጅቶ በመስራት ላይ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡
የተለያዩ የጥንቃቄ ተግባራት በመከናወን ላይ ናቸው የሚሉት የአስተዳደሩ ከንቲባ አቶ ጌቱ ቅጣው ማህበረሰቡ የባለሙያዎቹ ተማጽኖ ተሰምቶት ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ ራሱን እንዲጠብቅና እነሱም ሙያዊ ግዴታቸውን መወጣታቸውን እንዲቀጥሉ ጠይቀዋል፡፡