የአፍና አፍንጫ ጭምብል ማድረግ አስገዳጅ መሆኑን ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስታወቀ
የአፍና አፍንጫ ጭምብል ማድረግ አስገዳጅ መሆኑን ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስታወቀ
የኮሮና ቫይረስ ስርጭትን ለመግታት የተለያዩ እርምጃዎችን እወሰደ ያለው መንግስት፤ የአፍና የፊት መሸፈኛ ጭንብል (ማስክ) ማድረግ አስገዳጅ ለማድረግ መመሪያ መውጣቱን ጠቅላይ አቃቤ ህግ አስታውቋል፡፡
ጠቅላይ አቃቤ ሕጓ አዳነች አቤቤ በይፋዊ የፌስቡክ ገጻቸው “ከዛሬ በኋላ የፊትና አፍንጫ መሸፈኛ ጭምብል (ማስክ) ማድረግ ግዴታ” መሆኑን ጽፈዋል፡፡
ይህንን ለማስፈጸም የሚያስችል መመሪያ መጽደቁን የገለጹት አዳነች አቤቤ “ለእራስ፣ ለቤተሰብ፣ ለወገን እና ለሀገር በማሰብ ከሌሎች ስህተት በመማር ጥንቃቄን ከበፊቱ በበለጠ ማጠናከር” እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
የኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ መጋቢት 4 በአዲስ አባባ በአንድ ጃፓናዊ ላይ መገኘቱ ከተረጋገጠ በኋላ መግስት የቫይረሱን ስርጭት ለመከላከል በርካታ እርምጃዎችን ወስዷል፡፡
ከውጭ የሚመጡ መንደኞችን ወደ ለይቶ ማቆያ እንዲገቡ፤ ህዝብ የሚበዛባቸውን ስብሰባዎችን መሰረዝና ባርና ሬስቶራንቶች የሚሰሩበትን ሰአት መገደብ መንግስት ቀደም ብሎ የወሰዳቸው እርምጃዎች ናቸው፡፡
ከጎረቤት ሀገራት በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች በየብስ ወደ ኢትዮጵያ እንዳይገቡ በማሰብም መንግስት ሀሉንም ኢትዮጵያን ከጎረቤት ሀገራት የሚያዋስኗትን ድንበሮች ዝግ አድርጎ ቆይታለች፡፡
በኢትዮጵያ እስካሁን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች ቁጥር 731 ሲሆን ከእነዚህ ውስጥ 6 ሰዎች ህይወታቸውን አጥተዋል፡፡
የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ መንግስት እስከ ሀምሌ ድረስ የሚቆይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲያውጅ ያደረገው ሲሆን “ምርጫ 2012” ም እንዲራዘም ምክንያት ሆኗል፡፡