ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ተጨማሪ ውሳኔዎች አስተላለፉ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ከኮሮና ቫይረስ ጋር በተያያዘ ተጨማሪ ውሳኔዎች አስተላለፉ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኮቪድ-19ን ለመከላከል ከተቋቋመው ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች የተውጣጣ ኮሚቴ ጋር በኢንተርኔት አማካኝነት ያለውን የክንውን ሁኔታ እና ተጨማሪ መመሪያዎች እንዲሁም ኮቪድ-19ን ለመከላከል እና ስርጭቱን ለመግታት እየተወሰዱ ያሉ እርምጃዎችን አስመልክቶ ውይይት አድርገዋል፡፡
የኮሮና ቫይረስ በዓለም ላይ እያደረሰ ያለውን ፈታኝ ሁኔታ ኢትዮጵያ ለመቋቋም እንዲቻላት የሚከተሉት መመሪያዎች እና ተጨማሪ እርምጃዎች ተግባራዊ እንዲሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ውሳኔ አስተላለፉ።
1. ከዛሬ ከሰዓት ጀምሮ ወደ አዲስ አበባ የሚደርሱ እና ለይቶ ለመከላከያ በተዘጋጁት ሆቴሎች ለመቆየት አቅም የሌላቸው መንገደኞች ወደ አዳማ ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲ ተዘዋውረው ለ15 ቀናት እንዲቆዩ የወጣው መመሪያ ተግባራዊ እንዲያደርጉ
2. ከዛሬ አንስቶ ለተጨማሪ ሁለት ሳምንታት ከፍተኛ የትምህርት ተቋማትን ጨምሮ ትምህርት ቤቶች ተዘግተው እንዲቆዩ
3. በገበያ ስፍራዎች እና በሃይማኖት ተቋማት ውስጥ አካላዊ ርቀትን መጠበቅ ተፈፃሚ እንዲደረግ፤ በፌዴራል መንግሥት አስከፊ ብሔራዊ አደጋ በሚከሰት ጊዜ ሃይማኖታዊ ስብሰባዎች እንዲቋረጡ የማድረግ ሕገ-መንግሥታዊ መብት አለው። ሆኖም በሕገ-መንግሥቱ የተደነገጉት እርምጃዎች ተግባራዊ ከመደረጋቸው በፊት ዜጎች አካላዊ ርቀት የመጠበቅን መመሪያ ተግባራዊ እንዲያደርጉ
4. ሁኔታው ተጨማሪ ድጋፍን የሚጠይቅ ከሆነ ሁሉም ጡረታ የወጡ እንዲሁም በትምህርት ላይ ያሉ የሕክምና ባለሙያዎች ለብሔራዊ ግዳጅ እንዲዘጋጁ
5. የተለያየ መጠን እና ዓይነት ያላቸው መገልገያዎችን ያየዙ ከ134 በላይ ተቋማት ተለይተው መከላከያ፣ ለይቶ መቆያ እና ለሕክምና እንዲሆኑ ተለይተዋል። ስለዚህ ሁሉም ዜጎች አልጋዎች፣ ፍራሾች፣ አንሶላዎች፣ የመተንፈሻ ቬንትሌተሮች እና ሌሎች መገልገያዎችን ለማሰባሰብ በመሥራት ላይ የሚገኘውን ብሔራዊ የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴን ጥረት እንዲደግፉ ጥሪ አቅርበዋል።
6. የማክሮ-ኢኮኖሚ ንዑስ ኮሚቴው የኢኮኖሚ ዘርፉን ደህንነት ለማስጠበቅ የሚያስችሉ አማራጮችን ለመቀየስ በልዩ ልዩ ዘርፍ ከተሰማሩት አበይት የኢንዱስትሪ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት ሲያካሂድ ቆይቷል። ይህንን ተከትሎ ኢኮኖሚውን ለማረጋጋት የሚከተሉት እርምጃዎች ተፈፃሚ ይሆናሉ፡-
• የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያስፈልጉ የገቢ ዕቃዎች እና ግብዓቶች ከቀረጥ ነፃ እንዲገቡ ይደረጋል
• የፋይናንስ ዘርፉን ጤንነት አስጠብቆ ለማስቀጠል እና ባንኮች በኮሮና ቫይረስ ለተጎዱ ደንበኞቻቸው ጊዜያዊ የብድር እፎይታ እና ተጨማሪ ብድር ለመስጠት እንዲያስችላቸው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ተጨማሪ 15 ቢሊዮን ብር ለግል ባንኮች ያቀርባል።
• የውጭ ምንዛሬ የሚያስፈልጋቸው እና የኮቪድ-19 ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያስችሉ ዕቃዎች እና ግብዓቶችን ወደ ሀገር ውስጥ ለሚያስገቡ አስመጪዎች ባንኮች ቅድሚያ በመስጠት እንዲያስተናግዱ፤
• በፋይናንስ አገልግሎት የተነሳ ገጽ ለገጽ መገናኘት እና የብር ንክኪን ለመቀነስ እንዲቻል፣ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ በሞባይል አማካኝነት የሚደረግ ክፍያ እና ገንዘብ የማስተላለፍ ጣሪያውን ከፍ ያደርጋል፡፡
• የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ለውጭ ገበያ በሚቀርብ አበባ ላይ የጣለው ዝቅተኛ የመሸጫ ዋጋ ገደብ በጊዜያዊነት
እንዲነሳ ተደርጓል፡፡
• ኩባንያዎች የተሻለ የገንዘብ ፍሰት እንዲኖራቸው ለማስቻል፣ የገቢዎች ሚኒስቴር የተጨማሪ እሴት ታክስ አመላለስ ሂደቱን በተለየ መልኩ እንዲያፋጥን ይደረጋል፡፡
• የኮቪድ-19ን ወረርሽኝ ተከትሎ ሊከሰት የሚችለውን የሸቀጦች እጥረት እና አላስፈላጊ የዋጋ ጭማሪ ለመቆጣጠር በንግድና ኢንደስትሪ ሚኒስቴር የጀመረው ሥራ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡