የብልፅግና ፓርቲ 2ኛ መደበኛ ጉባኤ በምን ጉዳዮች ላይ እየተወያየ ነውʔ
ትናንት የተጀመረው የብልፅግና ፓርቲ 2ኛ መደበኛ ጉባኤ ዛሬም ቀጥሎ እየተካሄደ ነው
"ከቃል እስከ ባህል" በሚል መሪ ቃል እየተካሄደ ያለው ጉባዔው ውሳኔዎች ያሳልፋል ተብሎ ይጠበቃል
የብልፅግና ፓርቲ 2ኛ መደበኛ ጉባኤውን እያካሄደ ይገኛል።
ትናንት የተጀመረው የብልፅግና ፓርቲ 2ኛ መደበኛ ጉባኤ ዛሬም ቀጥሎ እየተካደ ሲሆን፤ በሁለተኛ ቀን ውሎው በልዩ ልዩ አጀንዳዎች ላይ እየተወያየ ይገኛል።
የፓርቲው ፕሬዚዳንት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በዛሬው ውሎ፤ የፓርቲውን የአምስት ዓመታት ጉዞዎች የዳሰሱ ሲሆን፤ በቀጣይም ፓርቲው ሊያካናውናቸው ያሰባቸውን ጉዳዮች አመላክተዋል።
ፓርቲው ሁለተኛ መደበኛ ጉባኤ በዛሬው እለት ጊዜው በጉባኤው አዘጋጅ አብይ ኮሚቴ ሪፖርት እና በሁለተኛው ጉባኤ የስብሰባ ሥነ-ሥርዓት ደንብ ላይ ተወያይቶ ማጽደቁን ከፓርቲው ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።
በቀጣይ መርሀ ግብሩም በቀሪ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎች ያሳልፋል፣ ቀጣይ አቅጣጫዎችንም ያስቀምጣል ተብሎ ይጠበቃል።
የብልጽግና ፕሬዝዳንት ጠቅላይ ሚንስትር ዐቢይ አሕመድ ትናንት በጉባዔው መክፈቻ ላይ ባደረጉት ንግግር፤ “ብልጽግና ሀገር በቀል እሳቤ ነድፎ የመጣ የመጀመሪያው ፓርቲ ነው” ብለዋል።
“በኢትዮጵያ የፓርቲዎች ጉባኤ ታሪክ መላው የኢትዮጵያ ብሔር ብሔረሰብ ተወካይ ኖሮት የሚደረግ ጉባኤ የብልጽግና ፓርቲ ጉባኤ ብቻ ነው” ሲሉም ተናግረዋል።
“ብልፅግና ለኢትዮጵያ ፍቱን መድሀኒቱ መደመር ነው ብሎ ሲመጣ ላለፉት ስድስት አመታት ብልፅግናን መክሰስ እንጂ ማንም አማራጭ ሃሳብ ይዞ አለመምጣቱ የሚያሳዝን ነው” ብለዋል።
ሃሳብ የነጠፈበት አካባቢ ማፍረስ ቢቀልም መልሶ መገንባት ግን መከራ ይሆናል ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ለዚህም አማራጭ የፖለቲካ ሃሳብ ቢፈጠር ለመማር ዝግጁ ነን ብለዋል።