“እኛ አሸባሪ ያልነውን ቡድን ተግባር አቅልለው የተመለከቱ አጋሮቻችን ዲፕሎማሲያዊ ጫና እያደረጉብን ነው”-ብልፅግና ፓርቲ
የፓርቲው ስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ ወቅታዊ ሃገራዊ ጉዳዮችን የተመለከተ ዝርዝር መግለጫን አውጥቷል
“የሃገር ውስጥ ጉዳዮቻችንን በውይይት ልንፈታ ብንችልም የውጭ ፈተናው ግን ጊዜ የሚሰጠን አይደለም” ሲልም ነው ብልጽግና ያስታወቀው
ኢትዮጵያ የዲፕሎማሲ አጋሮቼ ናቸው ከምትላቸው አካላት ጫና እየደረሰባት እንደሆነ የብልፅግና ፓርቲ ገለፀ፡፡
የፓርቲው ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ለሁለት ቀናት ሲያካሂድ የቆየውን ስብሰባ በተመለከተ ባወጣው መግለጫ “ወቅቱ ኢትዮጵያውያን በሁለት ጉዳዮች ላይ በጽናት ሊቆሙ የሚገባበት ጊዜ ነው” ብሏል፡፡ እነሱም የውስጥና ውጭ ጉዳዮች መሆናቸው በመጠቆም፡፡
ፓርቲው የውስጥ ጉዳዮቻችን በክርክር ፣ በልሂቃን ድርድር እና በውይይት የምንፈታቸው ናቸው የውጭ ፈተና ግን ጊዜ የሚሰጠን አይደለምም ነው ያለው::
የመርከቧ ተሳፋሪዎች በከራከርና መፎካከር የሚችሉት መጀመርያ መርከቧ ካለች ብቻ ነው ያለው የፓርቲው መግለጫ “እየሰጠሙ መብትም፣ ውይይትም፣ ክርክርም፣ ድርድርም፣ ትብብርም ፉክክርም የሚባል ነገር የለም” ሲልም አክሏል፡፡
ብልጽግና ፓርቲ የኢትዮጵያን ስልጣኔ ማየት የማይፈልጉ አካላት ዋና ዓላማቸውም ደካማ ኢትዮጵያን መፍጠር እንደሆነም ገልጿል፡፡
ኢትዮጵያን ከጎረቤቶቿ ጋር በጦርነት መማገድ፣ የኢትዮጵያን ኢኮኖሚ ማዳከም እንዲሁም ኢትዮጵያውያን በአካባቢና በእምነት ማጋጨት ኢትዮጵያ ጠል ኃይሎች የሚጠቀሙባቸው ሶስት መንገዶች መሆናቸውን በመጠቆም፡፡
መግለጫው ኢትዮጵያ በታሪኳ ከባእድ ኃይሎች የተቃጣባትን ወረራ ለመመከት በርካታ ጦርነቶች ማካሄዷንና የጦርነቶቹ ዋና ዓላማ ሀገሪቱ ፋታ አግኝታ ወደ ስልጣኔ እንዳትገሰግስ የማድረግ እንደነበርም አስገንዝቧል፡፡
የተካሄዱ ጦርነቶች ኢትዮጵያን ከማድከማቸው በሻገር የኢትዮጵያን የንግድ መስመሮች በመያዝ ሀገሪቱ ከባህር በር ውጭ እንድትሆን እንዲሁም ዓለም አቀፍ ብድር አግኝታ ታላላቅ ፕሮጀክቶችን እንዳታካሂድ እንቅፋት በመሆን ኢኮኖሚያዊ እድገቷ ለመሰናከል ጥረት መደረጉንም ጭምር፡፡
የዓባይ ግድብም ሆነ ሌሎችን ፕሮጀከቶች ለመገንባት ኢትዮጵያ በታሪኳ ለመገንባት ያደረገቻቸው ጥረቶች አለመሳካታቸንም እንደ አብነት በማንሳት፡፡
ለውጡን ተከትሎ የሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያ እና የፖሊሲ ነፃነትን ለማስጠበቅ የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎች ሲደረጉ ቆይተዋል ያለው ፓርቲው ዲፕሎማሲ ጫና እየደረሰበት መሆኑንም አስታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ ላይ ሁለንተናዊ ጫና ለመፍጠር በአብአዊ ድጋፍ ስም እንዲሁም በሰብአዊ ጥሰት ስም ተፅእኖ እየተደረገ ነውም ብሏል፡፡
“እኛ በአሻባሪነት ለመፈረጅ የተገደድንበት የጁንታው የጥፋት እንቅስቃሴ የዲፕሎማሲ አጋሮቻችን በቀላሉ ተመልክተው ጫና ሲያደርጉብን ይታያል” ሲልም አክለዋል ብልፅግና ፓርቲው ፡፡
የዓባይን ፕሮጀክት ወደ ፍፃሜ ማድረሳችን፣ በቀይ ባህር የነበረንን ተፅእኖ ፈጣሪነት ለመመለስ ተግተን መስራታችን፣ ከኤርትራ ጋር ነበረውን ግንኙነት አድሰን ቤተሰባዊነት መመስረታችን ፣ የጁንታውን ጦርነት በአሸናፊነት መወጣታችን ፣ የራሳችን የአኮኖሚ ማሻሻያ መንደፋችን፣አንድነትን በማቀንቀን ወደ ጠንካራ ሀገርነት መጓዛችን እየደረሱብን ላሉ ጫናዎች ምክንያቶች ናቸውም ብሏል የብልጽግና ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ በመግለጫው፡፡