የግድቡን 2ኛ ዙር ሙሌት ለማደናቀፍ በ37 ሺህ ኮምፒውተሮች ላይ ተነጣጥሮ የነበረ የሳይበር ጥቃት ማከሸፍ ተችሏል- ዶ/ር ሹመቴ ግዛው
በ2013 ዓ.ም ከ2 ሺህ 800 በላይ የሳይበር ጥቃቶች በኢትዮጵያ ላይ ተሰንዝረዋል
ህወሓት ከጥቅምት 24 በፊትም፤ በኋላም ከፍተኛ የሆኑ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎችን ሲያደርግ መቆየቱን ዶ/ር ሹመቴ ገልጿል
የታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌትን ለማደናቀፍ በ37 ሺህ ኮምፒውተሮች ላይ ተነጣጥሮ የነበረ የሳይበር ጥቃትን ቀድሞ ማከሸፍ መቻሉን የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ (ኢንሳ) ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሹመቴ ግዛው አስታወቁ።
ዶ/ር ሹመቴ ግዛው ከአል ዐይን አማርኛ ጋር በነበራቸው ቆይታ፤ ታላቁ የኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብ ታላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክት መሆኑን ጠቅሰው፤ በግድቡ ላይ የተለያዩ ሀገራት የተለያዩ ፍላጎት ስላላቸው በቀጥታ እና በተዘዋዋሪ ሙከራዎችን ያደረጉ ነበር ብለዋል።
ከዚህም ውስጥ ሌሎች ተቋማትን ኢላማ አድርጎ የህዳሴ ግድብን 2ኛ ዙር ውሃ እንዳይሞላ ሲደረግ የነበረ ሙከራን ለአብነት አንስተዋል።
በተለይም ሳይበር ሆረስ ግሩፕ በ2012 ዓ.ም የመጀመሪያው ዙር የውሃ ሙሌት ላይ እንዲሁም በ2013 ሁለተኛ ዙር የውሃ ሙሌት ወቅት በኢትዮጵያ ውስት የሚገኙ ኮምፒውተሮችን በመለየት ጥቃት ለማድረስ ሙከራዎችን ሲያደርግ እንበረ ለአብነት አንስተዋል።
ይህ ቡድን በኢትዮጵያ ሲስተም ውስጥ የነበሩ ከ37 ሺህ በላይ ኮምፒውተሮችን ለማጥቃት ተዘጋጅቶ እንደነበረ እና የኢንፎርሜሽን መረብ ደህንነት ኤጀንሲ የኢንተለጀንስ ቡድን ቀድሞ ማስጣሉንም ጠቅሰዋል።
ኢትዮጵያ የህዳሴ ግድብን ጨምሮ ለሌሎች የሜጋ ፕሮጀክቶቿ ልዩ ትከረት በመስጠት ክትትል እና ቁጥጥር እንደምታደርግም ዶክተር ሹመቴ አክለው አስታውቀዋል።
በ2013 ዓ.ም ኢትዮጵያ ምን ያክል የሳይር ጥቃት ሙከራዎችን አስተናግዳለች?
ማንኛውም ወደ ዲጂታል፣ ወደ ሳይበር እና ወደ ኔትዎርክ ጉዞ በተደረገ ቁጥር የሳይበር ጥቃቶች በዛው ልእ እያደጉና ተጋላጭነትም በዛው ልክ እየጨመረ እንደሚሄድ የኢንሳ ዋና ዳይሬክተር ዶ/ር ሹመቴ ግዛው ይናገራሉ።
የሳይበረ ጥቃቶችን እንደ አንድ ሀገራዊ ጉዳይ ብቻ አድርገን አንመለከትም ያሉት ዶከተር ሹመቴ፤ ምክንያቱም “ኢትዮጵያ የተያያዘችው ከዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ጋር ስለሆነ ተጠቃሚነታችን ባደገ ቁጥር ተጋላጭነት እያደገ ይሄዳል፤ እኛም በዛው ልክ ዝግጁነታችን እያደገ ይሄዳል” ሲሉም ተናግረዋል።
“ሌላው ዓለም ላይ ያሉ ስጋቶች በሙሉ ወደ ኢትዮጵያ ሊመጡ የማይችሉበት ሁኔታ የለም፤ ስለዚህም የሳይበር ጥቃቶች፣ ሙከራዎች እና ተጋላጭነቶች ከዓመት ወደ ዓመት እያደጉ መጥተዋልም ብለዋል፡፡
በ2013 ዓ.ም በኢትዮጵያ ላይ የተደረጉ የሳይበር፣ ሙከራዎች ስለላዎች እና ጥቃቶች ከ2012 እና ከዛ በፊት ከነበሩት ዓመታት በጣም እያደገ መምጣጡንም ዋና ዳይሬክተሩ ለአል ዐይን ተናግረዋል።
ለዚህም የተለያዩ ምክንያቶች መኖራቸውን በመጥቀስ፤ ከእነዚህም አብዛኛው ነገሮች ወደ ዲጂታል መሄድ፣ በዓለም አቀፍ ደረጃ የተከሰተው የኮቪድ 19 እንዲሁም ቀጠናዊ እና ሀገራዊ ጉዳዮች ተጠቃሽ ናቸው ብለዋል።
ምርጫ 2013 ተከትሎ ሙከራዎች እንደነበሩ ያነሱት ዶክተር ሹመቴ፤ ከሕዳሴ ግድብ 2ኛ ዙር የውሃ ሙሌት ጋር በተያያዘም በሳይበር አማካኘነት ጫናዎች ሲፈጠሩ እንደነበሩም አስታውቀዋል።በእነዚህ እና ከሌሎች ዓለማቀፋዊ ጉዳዮች ጋር ተደማመሮ በ2013 ዓ.ም በኢትዮጵያ ላይ የተደረጉ የሳይበር ሙከራዎች በዕጥፍ መጨመሩንም ነው የገለፁት።
በዓመቱ በሚሊየን የሚቆጠሩ የሳይበር ሙከራዎች እና ስለላዎች በኢትዮጵያ ላይ እንደሚፈፁሙ በመገልጽ፤ ነገር ግን ቢከሰቱ ትልቅ ጥፋት ሊያደርሱ ይችላሉ በሚል ተቋሙ የሚለካበት የራሱ የሆነ አሰራር እንዳለውም አስታውቀዋል።
በዚህ አግባብ ሲለካ በ2013 ዓ.ም በኢትዮጵያ ላይ ከ2 ሺህ 800 በላይ የሳይበር ጥቃቶች መሰንዘራቸውን ያሳታወቁ ሲሆን፤ ይህም በ2012 ዓ.ም ከደረሰው 1 ሺህ 80 አካባቢ ጥቃቶች ጋር ሲነጻጸር በእጥፍ መጨመሩን ያመላክታል ብለዋል።
ከእነዚህም አብዛኛዎቹን ማቅስቆም፣ መቀልበስ እና መከላከል ተችሏል ነው ያሉት ዋና ዳይሬክተሩ፤ እነዚህ ጥቃቶች ቢደርሱ ኖሮ በሀገር፣ በተቋማት እና በመንግስት ደረጃ ሊያደርሱ የሚችሉት የኢኮኖሚ፣ የፖለቲካ፣ የዲፕሎማሲ፣ የስነ ልቦና እና የማህበራዊ የስነ ተግባቦት ክስረት ከፍተኛ እንደነበረም ገልጸዋል።
ህወሓት እና የሳይበር ጥቃት ሙከራዎች…
“አሸባሪው” የህወሓት ቡድን በሀገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት ከፈጸመበት ጥቅምት 24 2013 ዓ.ም በፊትም ሆነ በኋላም ቢሳካለት “ኢትዮጵያን አፈርሳለው” የሚለውን ህልሙን እውን ለማድረግ በአካል ጦር ሜዳ ሄዶ ከመዋጋት ይልቅ የሳይበር ጥቃት ማካሄድ ነው ብለዋል ዶክተር ሹመቴ ከአል ዐይን ጋር በነበራቸው ቆይታ።
ህወሓት ይህንን ለማሳክት የሀሰት መረጃዎችን ከማሰራጨት ጀምሮ የተለያዩ አካላትን በመቅጠር ከፍተኛ የሆኑ የሳይበር ጥቃት ሙከራዎችን ሲያደርግ መቆየቱን አስታውቀዋል።
የሳይበር ጥቃቶች ጥቅምት 24 ቀን 2013 ዓ.ም ላይ እንዲሁም ከዚያን እለት በፊትም የነበሩ እና አሁንም የቀጠሉ መሆናቸውን ነው ዋና ዳይሬክተሩ የተናገሩት።
ከህወሓት ውጪም ሌሎች የሽበር ቡድኖች ኢትዮጵያ ላይ የሳይበር የሽበር ሙከራዎችን ይሰነዝራሉ፤ ነገር ግን በሳይበር ደህንነት ውስጥ ሁሌም ቀድሞ መገኘት ወሳኝ ስለሆነ፤ ኢትዮጵያም በዚህ መልኩ ጥቃቶችን ለመከላከል እየሰራች ነው ብለዋል።
ቴሌኮም ማጭበርበር
ከቴሌኮም ጋር በተያያዝ ከውጭ ሀገራት እና ከሀገር ውስጥ የተለያዩ ማጭበርበሮች እና የጥቃት ሙከራዎች እንደሚደረጉ ያነሱት ዶ/ር ሹመቴ፤ አሁን ላይ ግን በተሰሩ ስራዎች በከፍተኛ ሁኔታ የመቀነስ አዝማሚያ እያሳየ መምጣቱን አስታውቀዋል።
በተለይም ከዓመት ዓመት ከፍተኛ ቅናሽ እያሳየ መምጣቱን እና ምንም እንኳ በቁጥር ባያሥቀምጡም በ2012 ዓ.ም የነበረው ከዘንድሮ 2013ዓ.ም ጋር ሲነጻፀር ከፍተኛ ቀናሽ ማምጣቱን እና በ2014 ወደ ዜሮ ለማውረድ በእቅድ እንደሚሰራ አስታውቀዋል።