ኤርትራ “ለብሔራዊ ደህንነቴያሰጋኛል” በሚል በድንበር አካባቢ ያሉ የኢትዮጵያ ቦታዎች መያዟን ጠ/ሚ ዐቢይ ገለጹ
“ሕወሓት ማለት በነፋስ ላይ የተበተነ ዱቄት ማለት ነው” ሲሉ ጠ/ሚኒስትሩ ተናግረዋል
“የአማራ ልዩ ኃይል የፌደራሉ መንግስት ጠይቆት ነው ወደ ህግ ማስከበር ዘመቻው የተቀላቀለው” ብለዋል ጠ/ሚ ዐቢይ
“ከውጊያው በፊት እንደምናሸንፍ ለሕወሓት ከፍተኛ አመራሮች ነግሬያቸው ነበር” ሲሉ ጠቅላይ ሚኒሰትር ዶክተር አብይ አህመድ ተናገሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ ከሕወሓት ጋር ጦርነቱ ከመጀመሩ በፊት በተደጋጋሚ ጥሪ ማድረጋቸውን እና በሚስጥርም አስታራቂ ሽማግሌዎችን ልከው እንደነበር ተናግረዋል።
ጦርነቱ እንዳይኖር ተደጋጋሚ ጥረት ቢደረግም ማስቀረት እንዳልተቻለ ተናግረዋል።
1 ነጥብ 8 ሚሊዮን የትግራይ ህዝብ ላለፉት 20 ዓመታት በምግብ ዋስትና ፕሮግራም (ሴፍቲኔት) ታቅፎ ሲረዳ እንደነበር እና ከዚህ በተጨማሪ አንበጣ፣ ኮሮና ቫይረስ እና የጎርፍ አደጋ ባለበት ሕወሓት አስቀድሞ ጦርነት ለመጀመር ማሰቡን ኃላፊነት የጎደለው ሀሳብ እና ተግባር ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኮንነዋል።
ሕወሓት በአንድ ጊዜ በ200 ቦታዎች የሰሜን እዝ የአገር መከላከያ ሰራዊት ላይ ጥቃት መፈጸሙን አስታውሰው ከ7 ሺህ በላይ ወታደራዊ አመራሮች በህወሀት ተይዘው እንደነበር ጠቅላይ ሚኒስተሩ ገልጸዋል፡፡
በመላው ትግራይ ከ30 ሺህ በላይ እስረኞች በሕወሓት ተፈተው የተለቀቁ ሲሆን ከነዚህም ከ10 ሺህ በላይ የሚሆኑት በመቀሌ ከተማ ብቻ ተፈተው የተለቀቁ መሆናቸውን የተናገሩት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሕወሓት ይሄንን ያደረገው ክልሉን ለማተራመስ ካለው ፍላጎት እንደሆነ ገልጸዋል።
በትግራይ ክልል እየተካሄደ ያለው የህግ ማስከበሩ 3 አላማ ነበረው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስተሩ ወንጀለኞችን ወደ ህግ ማቅረብ፤ ታጋቾችን ማስለቀቅ እና የትግራይ ክልል ህዝብን ከሕወሓት አስተዳድር በማላቀቅ ጊዜያዊ አስተዳደር መመስረት ነው ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ሕወሓት ማለት በነፋስ ላይ የተበተነ ዱቄት ማለት ነው” ካሉ በኋላ “እሱን ሰብስበን ዱቄት ማድረግ አንችልም” በማለት ሕወሓት በፍጹም ወደ ቀድሞ ህልውናው ሊመለስ እንደማይችል አብራርተዋል፡፡ ከዚህ በኋላ የሚያዋጣው “ትግራይን በወጣቶች በምሁራን እንደገና ማደራጀት ነው ፤ ክልሉን አረጋግቶ ወደፊት መሄድ ነው ህዝባችን እየተጎዳ ስለሆነ”ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
በጦርነቱ የኤርትራ እና የአማራ ልዩ ኃይል ተሳትፎ ጉዳይ
ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በትግራይ ክልል የነበሩ የህግ ማስከበር ስራዎችን በጋራ ሊገመግሙ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል፡፡
የኤርትራ ወታደር በትግራይ ክልል በሴቶች ላይ ጥቃቶችን ፈጽሟል መባሉን ሪፖርት ለኤርትራ መንግስት አቅርበን የኤርትራ መንገስትም ችግሩ ካለ እርምጃ እንወስዳለን ማለቱን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል።
በቅርቡም ኢትዮጵያ እና ኤርትራ በትግራይ ክልል ያለውን የህግ ማስከበር ዘመቻ የሚገመግም የጋራ መድረክ እንዲኖር ለማድረግ እየሞከሩ መሆኑን ተናግረዋል።
በድንበር አካባቢ “የኤርትራ ወታደር በኢትዮጵያ ክልል ላይ መኖሩን” ያነሱ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኤርትራ የብሔራዊ ደህንነት ስጋት እንዳለባት በመግለጽ በድንበር አካባቢ ያሉ ቦታዎችን መያዟን እንደገለጸችላቸው ተናግረዋል። ይሁን እና የኢትዮጵያ ጦር ተመልሶ ምሽጉን ከተረከበ ጥለው እንደሚወጡ መግለጻቸውንም ነው ጠቅላይ ሚኒስትሩ የተናገሩት፡፡
በሴቶች ላይ የሚፈጸሙ ጥቃቶች በቋሚነት የሚቆሙት የህግ ማስከበር ስራው ተጠናቆ ሁለቱም አገራት ድንበራቸውን መጠበቅ ሲጀምሩ ነውም ብለዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማብራሪያቸው የአማራ ልዩ ሀይል መሬት ለማስመለስ ወደ ውጊያው አለመግባቱን ገልጸዋል።
ባለፉት 10 ዓመታት የወልቃይት ጉዳይ ሲነሳ የቆየ መሆኑን አስታውሰው “ሰራዊታችንን የት ጋር ማስፈር እንዳለብን የምንወስነው እኛ ነን” ብለዋል።
“የአማራ ልዩ ኃይል የፌደራሉ መንግስት ጠይቆት ነው ወደ ህግ ማስከበር ዘመቻው የተቀላቀለው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ልዩ ሀይሉ ያጠፋው ጥፋት ካለ እንደሌሎቹ የጸጥታ ኃይሉ አካላት ሁሉ በህግ ይጠየቃል ብለዋል። የአማራ ልዩ ሀይልን ችግር ካለብን በሌሎች ክልሎችም ልናስሰልፈው እንችላለንም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ።
አሁን ላይ ልዩ ሀይሉ የህይወት መስዋዕትነት እየተከፈለ መሆኑንም የተናገሩ ሲሆን “የወልቃይት እና አካባቢው የመሬት ይገባኛል ጉዳይን የወሰን እና ማንነት ጉዳይ ኮሚሽን ምላሽ ይሰጥበታል” ብለዋል፡፡
የሰብዓዊ መብት ጥሰት
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መንግስት የህግ ማስከበር ዘመቻ ማካሄዱን ተከትሎ በትግራይ ክልል የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈፀሙን የሚያመላክቱ መረጃዎች አሉ ብለዋል፡፡
በመከላከያ በኩል ተፈጽመዋል የተባሉትን በተመለከተ ከመከላከያ ሠራዊት አባላት ጋር ለ7 ቀናት ግምገማ ማድረጋቸውን የጠቆሙ ሲሆን ሴቶችን የደፈረ እና ንብረት የዘረፈ የአገር መከላከያ ሠራዊት አባል ካለ በህግ እንደሚጠየቅም ጠቅላይ ሚኒስትሩ ገልጸዋል፡፡ “ጀግኖችን እንሾማለን አጥፊዎችን ደግሞ በህግ እንጠይቃለን” ሲሉም ነው የተናገሩት፡፡
“እኛ ወታደር የላክነው ጁንታውን እንዲቆጣጠር እንጂ እንዲደፍር አይደለም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒሰትሩ በዚህ ወንጀል የተሰማራ ወታደር በሕግ ተጠያቂ እንደሚደረግም ነው የተናገሩት፡፡
ከፍተኛ ግነት እና ፕሮፖጋንዳ አለ ግን አንድም ጥፋት ካለ አጥፊው ተጠያቂ ይደረጋል፤ ህዝቡ ላይ እየደረሰ ያለው ጉዳት ምክር ቤቱን ሊያሳስባቸው ይገባልም ብለዋል ጠቅላይ ሚኒስትሩ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሰሜን ዕዝ ፣ ማይካድራ ፣ በጎንደር ና ባህር ዳር ሕወሓት በፈጸማቸው የሮኬት ጥቃቶችም የደረሱ ጉዳቶችን እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን ጠቅሰዋል፡፡
ከጦርነቱ በኋላ መንግስት ለትግራይ ክልል ለሰብዓዊ ድጋፍ እና ለመሰረተ ልማት ግንባታ ከ 1 ቢሊዮን ዶላር (40 ቢሊዮን ብር) በላይ ወጪ ማውጣቱን የጠቆሙት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከድጋፍ አንጻር በየሚዲያው የትግራይ ጉዳይ እንደሚያሳስባቸው የሚገልጹ አካላት እዚህ ግባ የሚባል ድጋፍ አለማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
በአማራ ክልል በኦሮሚያ ብሄረሰብ ዞንና በሰሜን ሽዋ ዞን ስለተፈጠረው ችግር
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የፓርላማ አባላቱ ሰሞኑን ‘በኦሮምያ ልዩ ዞንና ሰሜን ሽዋ አካባቢ የተፈጠሩትን ግጭቶች’ በተመለከት የተለያዩ አስታየቶች መሰንዘራቸውን ተከትሎ ፣የፓርላማ አባላትን አስታየትን መነሻ በማድረግ “ማንም ሰው በሰፈር አስቦ ኢትዮጵያን ማሳነስ ካልሆነ ማሳደግ አይችልም” ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአማራ ክልል በኦሮሞ ብሔረሰብ አስተዳደር ዞን ጅሌ ጥሙጋና በሰሜን ሸዋ ዞን አጣዬ ስለተፈጠረው ግጭት በሰጡት ማብራርያ “አሁን በአማራ ክልል ግጭት የተከሰተበት አከባቢ በወሎ ክፍለ ሀገር የነበረ አንድ ህዝብ የነበረ ነው፣ የተጋባ ህዝብ ነው፣ ይህን ለመለያየት የሚደረገውን ስራ አጋዥ መሆን የለብንም፣ ይህ የጠላት ስራ ነው” ብለዋል፡፡
“ኦነግ ሸኔ (ሽፍታው) የት ነበረ ላለፉት 20 ዓመታት” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “300 የኦነግ ሸኔ የሰለጠኑ አባላትን ትግራይ ክልል አግኝተናል” ብለዋል፡፡ ትልቁ የኢትዮጵያ ነቀርሳና ካንሰር “ከሰፈር የዘለለ ነገር አለማሰብ ነው” ያሉት ጠቅላይ ሚኒሰትሩ የፓርላማ አባላቱ ከመሰል አስተሳሰቦች እንዲወጡም አሳስበዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒሰትሩ “ኦሮሞና አማራን ለማባላት ገንዘብና ጊዜ ሰጥተው የሚታገሉ እንዳሉ እያወቃችሁ ፣ በዚህ የተቀደደ ቦይ ውስጥ የምትገቡ ትገርሙኛላችሁ”ብለዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ኦሮሞና አማራ ከተጋደለ ኢትዮጵያ ሚባል ሀገር የለም” ያሉም ሲሆን የፖለቲካ ነጋዴዎችና አክቲቪስቶች ህዝቡን ከማጋጨት ድርጊታቸው እንዲቆጠቡና በሀገር ግንባታ የራሳቸውን አዎንታዊ አሻራ ሊያኖሩ ይገባል ሲሉም መክረዋል፡፡