የፕሬዚደንት ጆ ባይደን መልዕክተኛው ሴናተር ክሪስ ኩንስ በኢትዮጵያ ስኬታማ ጊዜ ማሳለፋቸውን ገለጹ
ተጽእኖ ሊያሳድሩ የሚፈልጉ አካላትን ለመመከት አፍሪካና ሩሲያ ግንኙነታቸውን ማጠናከር እንዳለባቸው ጠ/ሚ ዐቢይ ገልጸዋል
ጠ/ሚ ዐቢይ በትግራይ ጉዳይ ፣ ከሱዳን ጋር ስላለው ውዝግብ እና በሕዳሴው ግድብ ዙሪያ የሰጡትን ገለጻ ሴናተሩ በአዎንታዊነት ጠቅሰዋል
የአሜሪካ ፕሬዚደንት ጆ ባይደን ወደ ኢትዮጵያ ተልከው ፣ በኢትዮጵያ ለቀናት የቆዩት ሴናተር ክሪስ ኩንስ የኢትዮጵያ ቆይታቸው ስኬታማ እንደነበር ገልጸዋል፡፡
ሴናተሩ ወደ አሜሪካ ከተመለሱ በኋላ ከአሜሪካ ሴኔት የውጭ ግንኙነት ኮሚቴ ጋር በነበራቸው ስብሰባ ላይ ፣ በኢትዮጵያ ቆይታቸው ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ከሌሎች የኢትዮጵያ ከፍተኛ ባለስልጣናት እንዲሁም የዓለማቀፍ ድርጅቶች ኃላፊዎች ጋር መወያየታቸውን ተናግረዋል፡፡
ሴኔቱ ኢትዮጵያን በተመለከተ በሚያሳልፈው ውሳኔ ላይ ለውጥ ለማድረግ የሚያስችል ሀሳብ እንዲሰጡ በውጭ ግንኙነት ኮሚቴው እንደተፈቀደላቸው ጠቅሰው ለዚህም ምስጋና አቅርበዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በትግራይ ክልል ለተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የሚመለከታቸው አካላት ተጠያቂ እንደሚሆኑ መግለጻቸውን ፣ እንዲሁም በኢትዮጵያ ግዛት የኤርትራ ወታደሮች ስለመኖራቸው በይፋ መናገራቸውን ሴናተር ኩንስ በስብሰባው ላይ በአዎንታዊነት ጠቅሰዋል፡፡ ከሱዳን ጋር ላለው የድንበር ውዝግብ ዕልባት ለማምጣት እንዲሁም የታላቁን የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አለመግባባት ለመፍታት የኢትዮጵያን ዝግጁነትም በአዎንታዊነት ነው ሴናተሩ ያነሱት፡፡
ይሁንና “አሁንም መፈታት ያለባቸው ጉዳዮች አሉ” ያሉት ሴናተሩ እነዚህም “የተሟላ የሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽነት ፣ ግጭት ማቆም እና ነጻና ፍትሀዊ ምርጫ የማድረግ ሽግግር” መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ በነዚህ ጉዳዮች ላይ ከሴኔቱ ኮሚቴ ጋር በጋራ እንደሚሰሩ እና የተሻለ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ያላቸውን ተስፋም ገልጸዋል፡፡
በትግራይ ክልል የተካሔደውን ውጊያ ተከትሎ በአሜሪካ እና በኢትዮጵያ መንግስታት መካከል አለመግባባቶች መፈጠራቸው ይታወቃል፡፡
ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ ማክሰኞ መጋቢት 14 ቀን 2013 ዓ.ም በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ለሕዝብ ተወካዮች ም/ቤት አባላት በሰጡት ማብራሪያ ከሰብዓዊ ድጋፍ ተደራሽነት አንጻር ፣ እስካሁን የኢትዮጵያ መንግስት 4.2 ሚሊዮን ለሚሆኑ ዜጎች ድጋፍ ማድረሱን ገልጸው በትግራይ ያለው “የሰብዓዊ ሁኔታ ያሳስበናል” የሚሉ አካላት ግን ከወሬ ባለፈ እዚህ ግባ የሚባል ድጋፍ አለማድረጋቸውን ተናግረዋል፡፡
ከሕወሓት ኃይል ጋር የሚደረገውን ውጊያ በተመለከተ በሰጡት ማብራሪያ በወንጀል የሚፈለጉ ግለሰቦችን ለመያዝ ከሚደረገው ውጭ በክልሉ ያለው ዋናው ውጊያ ማለቁን ነው የገለጹት፡፡ ተሸሽገው የሚገኙ የሕወሓት አመራሮች ከዚህ በኋላ ወደ መሪነት ሊመጡ የሚችሉበት ህጋዊም ሆነ ሞራላዊ ዕድል እንደሌለም ተናግረዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትግራይ ክልል የሰብዓዊ መብት ጥሰት መፈጸሙን ፣ የኤርትራ ወታደሮች በኢትዮጵያ መኖራቸውን እና በወታደሮቹ የተፈጸሙ ወንጀሎችን ኢትዮጵያ እንደማትቀበል መግለጻቸውም ይታወሳል፡፡
የተባበሩት መንግስታት የጸጥታው ምክር ቤት በኢትዮጵያ ላይ እርምጃ እንዲወስድ አሜሪካ በተደጋጋሚ ያደረገችው ሙከራ በነሩሲያ ቡድን ተቃውሞ ውድቅ መደረጉ ይታወሳል፡፡ አሜሪካ ከትግራይ ክልል ጋር በተያያዘ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትሯ በኩል ያወጣቻቸውን መግለጫዎች “ጣልቃ የመግባት ሙከራ” በሚል ያጣጣለችው ኢትዮጵያ ሩሲያን ፣ ቻይናን እና ሕንድን ማመስገኗም ይታወቃል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በትናንትናው ዕለት በተካሔደ “የሩሲያ-አፍሪካ” አለም አቀፍ የፓርቲዎች ጉባኤ ላይ በበይነ መረብ ባደረጉት ንግግር “በጊዜ ሂደት የተፈተነውን የአፍሪካ እና የሩሲያ አብሮነት በማጽናት የህዝቦችን መሰረታዊ ጥያቄ ለመመለስ ተጽእኖ ሊያሳድሩ የሚችሉ አካላትን መመከት ያስፈልጋል” ብለዋል።
ሴናተር ኩንስ ከም/ጠ/ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር በነበራቸው ውይይት ወቅት “ኢትዮጵያ ሉዓላዊት ሀገር እንደመሆኗ መጠን በግዛቷ ውስጥ ለምታከናውነው ማንኛውም አይነት የህግ ማስከበር ዘመቻ ጣልቃ ገብነት እንደማትቀበል” አቶ ደመቀ መግለጻቸውን አምባሳደር ዲና መናገራቸው የሚታወስ ነው፡፡