በኮንሶ እና አሌ ህዝቦች መካከል እርቀሰላም የሚያስፈጽሙ የሀገር ሽማግሌዎች ቡድን ተቋቋመ
በግጭቱ ሚና ነበራቸው የተባሉ 7 አመራሮች በቁጥጥር ስር ዉለዋል
በመሬት ይገባኛል ግጭት 21ሰዎች በተገደሉበት የኮንሶ እና አሌ አዋሳኝ አካባቢ የደቡብ ክልል ር/መስተዳደር ጉብኝት አድርገዋል
በኮንሶ እና አሌ ህዝቦች መካከል እርቀሰላም የሚያስፈጽሙ የሀገር ሽማግሌዎች ቡድን ተቋቋመ
በደቡብ ክልል ኮንሶ ዞን እና አሌ ልዩ ወረዳ አዋሳኝ አካባቢዎች በይዞታ ይገባኛል ምክንያት ከሳምንት በፊት በተፈጠረ ግጭት ከሁለቱም ወገን 21 ሰዎች መሞታቸው ይታወቃል፡፡ በግጭቱ በርካታ ሰዎች ለጉዳት ሲዳረጉ በቤትና ንብረትም ላይ ከፍተኛ ጉዳት ደርሷል፡፡
የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር አቶ ርስቱ ይርዳው በዛሬው ዕለት በአካባቢው ተገኝተው ተጎጂዎችን ጎብኝተዋል፡፡
ምክትል ርዕሰ መስተዳደሩ ክክልሉ መንግስት ሌሎች ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች ጋር ባደረጉት ጉብኝት ከአካባቢው ህብረተሰብ ጋር ዉይይት ማድረጋቸውንም የደቡብ ክልል መንግስት ኮሙኒኬሽን ገልጿል፡፡
በዉይይቱ ላይ አቶ ርስቱ ይርዳው እንደገለጹት በሁለቱም አካባቢ የሚኖሩ ህዝቦች “ለህብረ ብሄራዊነታችን ተምሳሌት” የሆኑ መሆናቸውን በመጥቀስ ጥንት ያቆዩትን የአብሮነት እሴት እንዲያስቀጥሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ግጭቱ “የግል ፍላጎት ባላቸው አካላት” የተነሳ እና “የሁለቱን ህዝቦች ወንድማማችነት በማሻከር ጥቅም ማጋበስን ዓላማ ያደረገ” እንጂ የይዞታ ይገባኛል ጥያቄው በንግግር መፈታት እንደሚችል የዉይይቱ ተሳታፊዎች መናገራቸውን የክልሉ ኮሙኒኬሽን መረጃ ያመለክታል፡፡
የኮንሶ ዞን እና የአሌ ልዩ ወረዳ የሀገር ሽማግሌዎች እና ሌሎች የህብረተሰብ ክፍሎችም ችግሩን በጋራ ለመቅረፍ ቃል የገቡ ሲሆን “ሁለቱን ህዝቦች የሚለይ ሀይል እንደሌለ” ተናግረዋል፡፡
በኮንሶ ዞን እና የአሌ ልዩ ወረዳ መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት በመፍታት እርቀሰላም የሚያወርዱ የሀገር ሽማግሌዎች ቡድንም ርዕሰ መስተዳድሩ በተገኙበት መድረክ ተቋቁሟል፡፡
በአካባቢው የህግ የበላይነትን ለማረጋገጥ የተጀመሩ ተግባራት እንደሚቀጥሉ አቶ ርስቱ ገልጸዋል፡፡ እስካሁን ለግጭቱ መቀስቀስ እና መባባስ ምክንያት ናቸው ተብለው የተጠረጠሩ ሰባት አመራሮች በቁጥጥር ስር መዋላቸውም ይፋ ተደርጓል።