ከሲዳማ ክልል ዉጭ ያሉ የአደረጃጀት ጥያቄዎች በፌደሬሽን ም/ቤት በተያዘው መንገድ ምላሽ ያገኛሉ ተብሏል
ሲዳማ የኢትዮጵያ 10ኛው ክልል በመሆን ከነባሩ የደቡብ ክልል ስልጣን ተረከበ
የብሔራዊ ክልላዊ የሽግግር መስተዳድሮችን ለማቋቋም በሽግግር መንግስቱ ወቅት በወጣው አዋጅ ቁጥር 7/1984 መሠረት አምስት የነበሩ ክልሎች (ከክልል 7-11 ያሉት) ከህግ ውጭ ባልታወቀ መንገድ ከሁለት ዓመታት በኋላ ተሰባስበው አንድ ክልል እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡
እናም የደቡብ ክልል ምክር ቤት መረጃ እንደሚያመለክተው ከሰኔ 15 ቀን 1987 ዓ.ም ጀምሮ በአምስቱ ክልሎች ስብስብ ተመስርቶ ለረዥም ጊዜ የቆየው የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ከምስረታው ጀምሮ እስካሁን እንደየወቅቱ አንዴ ሞቅ ሌላ ጊዜ ቀዝቀዝ የሚሉ የአደረጃጀት ጥያቄዎችን በአንድነት ካቀፋቸው የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች እያስተናገደ ዛሬ ላይ ደርሷል፡፡
ከነዚህም ጥያቄዎች ጎልቶ የወጣው የሲዳማ ብሔር በክልልነት የመደራጀት ጥያቄ ከብዙ ዉጣ ዉረድ በኋላ በህዝበ ዉሳኔ (ሪፈረንደም) እልባት ካገኘ ወራት ተቆጥረዋል፡፡
የሲዳማን ዞን በክልል ደረጃ ለማደራጀት ኅዳር 10 ቀን 2012 ዓ.ም በተካሄደው ሕዝበ ውሳኔ ዞኑ የኢትዮጵያ 10ኛው ክልል ለመሆን በሕዝበ ውሳኔው ለመሳተፍ ከተመዘገበው ህዝብ ከሁለት ሚሊዮን በላይ የሚሆነውን ፣ማለትም 98.51 በመቶ ድምጽ ማግኘቱን የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በወቅቱ መግለጹ ይታወቃል፡፡
በ5ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 2ኛ አስቸኳይ ጉባኤው ዛሬ ከሰዓት በደቡብ ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልላዊ መንግስት በአዳዲስ መዋቅሮች ለመደራጀት በቀረበ ጥያቄ ፣ ምላሽ እና የውሳኔ ሀሳብ ላይ የመከረው የደቡብ ክልል ምክር ቤት ለአዲሱ የሲዳማ ክልል ስልጣን አስረክቧል፡፡
ከዚህ ቀደም የሲዳማን ክልል ምስረታ በተመለከተ ለአል ዐይን አማርኛ በስልክ ማብራሪያ የሰጡት የሲዳማ ዞን የህዝብ ግንኙነት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ገነነ አበራ ከሀምሌ 1 ቀን 2012 ዓ.ም ጀምሮ የአዲሱ ክልል አደረጃጀት ይፋ ሆኖ ስራ እንደሚጀምር ታቅዷል ብለዋል፡፡
የደቡብ ሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች የመዋቅር ጉዳይ
የሌሎች ብሔር ብሔረሰቦች የመዋቅር ጥያቄ በፌደሬሽን ም/ቤት በተያዘው መንገድ ምላሽ እንደሚያገኝ ተገልጿል፡፡
80 አባላት ያሉት “የሰላም አምባሳደር” ኮሚቴ ከደቡብ ክልል ብሔሮች እና ብሔረሰቦች ተወካዮች ጋር በተለያዩ ጊዜያት ዉይይት ካደረገ በኋላ ክልሉን በማፍረስ ይፈጠር ስላለው አዲስ አደረጃጀት የመጨረሻ የውሳኔ ምክረ ሀሳብ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅርቧል፡፡
ኮሚቴው ያቀረበው የአደረጃጀት የውሳኔ ሀሳብ የማህበረሰቡን ስነ ልቦና ፣ ቋንቋ ፣ መልክዓ ምድር (ጂኦግራፊ) እና የህዝቡን ዉሳኔ ታሳቢ ያደረገ እንደሆነ በውይይቱ ወቅት አስታውቋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፣ የብልጽግና አመራሮች እና የፌደሬሽን ም/ቤት ተወካዮች ፣ በቀረበው የውሳኔ ሀሳብ ላይ ፣ ከክልሉ ዞኖች እና ከልዩ ወረዳ የፖለቲካ አመራሮች ጋር ሰኔ 2 ቀን 2012 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ዉይይት አድርገዋል፡፡
በዚህም መሰረት ነባሩ የደቡብ ክልል ፈርሶ በአራት ክልሎች እና በአንድ ልዩ ዞን እንዲደራጅ የቀረበው ዉሳኔ ተቀባይነት ማግኘቱን አል ዐይን አማርኛ በውይይቱ ከተሳተፉ ግለሰቦች ማረጋገጥ ችሏል፡፡
በዚህም መሠረት አዲስ እንዲመሰረቱ ከቀረቡት ተጠባቂ ክልሎች አንዱ ጋሞ፣ ጎፋ፣ ኮንሶ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ደራሼ፣ ቡርጂ፣ አማሮ ፣ ባስኬቶ እና ኮንሶ ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች በአንድ ክልል ማለትም “ኦሞቲክ ክልል” ተብለው እንዲደራጁ ፤ በደቡብ ክልል ማዕከላዊ እና ሰሜናዊ አቅጣጫ የሚገኙት ሀዲያ ፣ ከምባታ ጠምባሮ ፣ስልጤ፣ ጉራጌ ፣ የም እና ሀላባ አንድ ላይ እንዲደራጁ ፤ ቀድሞ በህዝበ ውሳኔ ጉዳዩን የጨረሰው የሲዳማ ዞን ብቻውን እንዲደራጅ ፤ ከፋ፣ቤንች ማጂ፣ ሸካ እና ዳውሮ በአንድ ክልል እንዲደራጁ ፤ ጌዴኦ ደግሞ በልዩ ዞን እንዲደራጅ የውሳኔ ሀሳብ ቀርቧል፡፡ ይሁንና ጌዴኦ ከየትኛው ክልል ጋር እንደሚሆን የተገለጸ ነገር ባለመኖሩ ወደፊት እልባት እንደሚያገኝ ይጠበቃል፡፡
በዛሬው ዕለት ሰኔ 11 ቀን 2012 ዓ.ም የሲዳማ ክልል ጉዳይ የመጨረሻ እልባት ያገኘ ሲሆን የሌሎቹ ክልሎች አደረጃጀት ገና የሚቀሩት ሂደቶች አሉ፡፡
የቀረበው የመጨረሻ የውሳኔ ምክረ ሀሳብ በአንድ ወር ዉስጥ ዉሳኔ እንዲያገኝ ለፌደሬሽን ምክር ቤት ተመርቷል፡ ም/ቤቱም ሰኔ 3 ቀን 2012 ዓ.ም ባካሔደው 5ኛ ዓመት የሥራ ጊዜ 2ኛ መደበኛ ስብሰባ የክልልነት ጥያቄዎችን በተገቢው መንገድ ለማስተናገድ የጋራ መድረኮችን የማመቻቸት፣ የምክር ቤቱን አስፈጻሚ ከክልሎች አስፈጻሚዎች ጋር የማገናኘትና የማወያየት፣ ከዚህ ቀደም የተጠኑ ጥናቶችንና የሰላም አምባሳደሮችን ስራ እንዲሁም ሕዝብን በማወያየት የመጨረሻ ውሳኔ ለማሳለፍ የሚያስችል የውሳኔ ሃሳብ የሕገ መንግሥት ትርጉምና የማንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ይዞ እንዲቀርብ በምክር ቤቱ በአብላጫ ድምጽ ተወስኗል።
አጠቃላይ የአደረጃጀት ጥያቄው በአንድ ወር ጊዜ ዉስጥ ይጠናቀቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይሁን እንጂ ከተለያዩ ብሔሮች የሚነሱ ተጨማሪ ጥያቄዎች (በተለይም በተናጥል የመደራጀት እና አንዳቸው ከሌላኛቸው ጋር በአንድነት ላለመደራጀት መፈለግ) መኖራቸው ጉዳዩን እንዳያንዛዛው ያሰጋል፡፡