ምክር ቤቱ የሕገ መንግሥት ትርጉምና የማንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የመጨረሻ የውሳኔ ሃሳብ ይዞ እንዲቀርብ አዘዘ
ምክር ቤቱ የሕገ መንግሥት ትርጉምና የማንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የመጨረሻ የውሳኔ ሃሳብ ይዞ እንዲቀርብ አዘዘ
የብሔራዊ ክልላዊ የሽግግር መስተዳድሮችን ለማቋቋም በሽግግር መንግስቱ ወቅት በወጣው አዋጅ ቁጥር 7/1984 መሠረት አምስት የነበሩ ክልሎች (ከክልል 7-11 ያሉት) ከህግ ውጭ ባልታወቀ መንገድ ከሁለት ዓመታት በኋላ ተሰባስበው አንድ ክልል እንዲሆኑ ተደርጓል፡፡
በአምስቱ ክልሎች ስብስብ ተመስርቶ ለረዥም ጊዜ የቆየው የደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ከምስረታው ጀምሮ እስካሁን እንደየወቅቱ አንዴ ሞቅ ሌላ ጊዜ ቀዝቀዝ የሚሉ የአደረጃጀት ጥያቄዎችን በአንድነት ካቀፋቸው የተለያዩ ብሔር ብሔረሰቦች እያስተናገደ ዛሬ ላይ ደርሷል፡፡
ከክልሉ በመለየት ራስን ችሎ ለመደራጀት የሚነሱ ጥያቄዎች በኃይልም በድለላም ሲታፈኑ ስለመቆየታቸው ይነገራል፡፡ ይሁንና የህዝቡ የአደረጃጀት ጥያቄ ከቀደመው ጊዜ በተለየ ሁኔታ ገፍቶ በመምጣቱ ክልሉን በሚመለከት አዳዲስ ጥናቶች እና ዉሳኔዎች ተስተውለዋል፡፡ እናም ላለፉት 27 ዓመታት በአንድ ጎጆ ስር የነበሩት የደቡብ ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች በአዲስ መልክ በተለያየ አደረጃጀት መካለላቸው እውን ሊሆን ተቃርቧል፡፡
የአደረጃጀት ጥያቄዎች
በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች ክልል ዉስጥ የሚገኙ የተለያዩ ብሔሮች ሲያነሷቸው የነበሩትና ለዓመታት ሲንከባለሉ የቆዩት የአደረጃጀት ጥያቄዎች ይበልጥ ጎልተው የወጡት ከ2010 ዓ.ም ሀገራዊ ለውጥ በኋላ ነው፡፡ ይሄም ደቡብ ከለውጡ በኋላ ለረዥም ጊዜ መረጋጋት የተሳነው ክልል እንዲሆን ካደረጉት ምክንያቶች መካከል ዋነኛው ሆኖ ቆይቷል፡፡ ከለውጡ በኋላ የተፈጠረው የክልሉ አለመረጋጋት ደግሞ 2 የክልሉ ፕሬዝዳንቶች ከኃላፊነታቸው እንዲነሱ ምክንያት ሆኗል፡፡ የአሁኑን የክልሉ መሪ ጨምሮ ሶስት ርዕሰ መስተዳድሮች ተፈራርቀዋል፡፡
የሲዳማ ብሔር በክልልነት የመደራጀት ጥያቄ ከብዙ ዉጣ ዉረድ በኋላ በህዝበ ዉሳኔ (ሪፈረንደም) እልባት እንዲያገኝ መወሰኑ በክልልነት የመደራጀት ጥያቄዎች በስፋት እንዲነሱ ገፊ ምክንያት እንደሆነ ይታመናል፡፡ በክልሉ ምክር ቤት ዉሳኔ በቅርቡ በዞን ደረጃ የተደራጁትን እንደ ጎፋ ያሉ ዞኖች ጨምሮ በአጠቃላይ የሚነሱ የክልልነት እና የተለያዩ አደረጃጀት ጥያቄዎች ክልሉን ይመራ ለነበረው የደቡብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢሕዴን) ብቻ ሳይሆን ለፌደራሉ መንግስትም ከባድ ፈተና ሆኖበት ቆይቷል፡፡ በአጠቃላይ ሲዳማን ሳያካትት በክልልነት ለመደራጀት 14 ዞኖች በየዞናቸው ምክር ቤት በሙሉ ድምጽ አስጸድቀው ለክልሉ መንግስት በይፋ ጥያቄ ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡ በአጠቃላይ በክልሉ የሚነሱ የአደረጃጀት ጥያቄዎችን ለመመለስ የክልሉና የፌደራሉ መንግስት ጥናትን መሰረት ያደረጉ የተለያዩ እርምጃዎችን መውሰዳቸው ተገልጿል፡፡
የአደረጃጀት ጥያቄዎችን የመመለስ ሂደት
በደቡብ ክልል የሚነሱ የአደረጃጀት ጥያቄዎችን እያንዳንዳቸውን በተናጠል መመለስ አዳጋች መሆኑን የተረዳው የቀድሞው ደኢህዴን ፣ ጥያቄዎችን በጥናት ለመመለስ ወስኖ አጥኚ ቡድን በማቋቋም ባስጠናው ጥናት መሠረት ሦስት አማራጮችን አቅርቧል።
እነዚህም:-
1ኛ/ ክልሉን እንደነበረ ማስቀጠል ፤
2ኛ/ ክልሉን 1 ለ 55 ማደራጀት (ሲዳማን በመለየት 55ቱን ብሔር፣ ብሔረሰቦች በአንድነት ማስቀጠል) 3ኛ/ የክልልነት ጥያቄን ላልተወሰነ ጊዜ አግዶ ማቆየት የሚሉ ነበሩ፡፡
የዚህ ጥናት ውጤት ብዙም ሳይቆይ ከብልጽግና ፓርቲ መመስረት ጋር ተያይዞ ከጥቅም ዉጭ ሆኗል፡፡ በምትኩም በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የተዋቀረ 80 አባላት ያሉት “የሰላም አምባሳደር” የተሰኘ ኮሚቴ ተዋቅሮ የክልሉን ሕዝብ በማወያየት አዲስ ምክረ ሀሳብ ይዞ እንዲቀርብ ተደርጓል፡፡
ኮሚቴው በየዞኑና በየወረዳው እየተንቀሳቀሰ፣ ህብረተሰቡን በማወያየት፣ ፍላጐቱን አድምጦ የዳሰሳ ጥናት አድርጓል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) የኮሚቴውን ጥናት ተከትሎ ከክልሉ የተለያዩ ዞኖችና ወረዳዎች የተውጣጡ የየማህበረሰቡ ተወካዮችን እና የፖለቲካ አመራሮችን በተለያዩ ጊዜያት በጽ/ቤታቸው ማወያየታቸው ይታወቃል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ግንቦት 4 ቀን 2012 ዓ.ም ከደቡብ ክልል የዞን አመራሮች ጋር ዉይይት ካደረጉ በኋላ በፌስ ቡክ ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ “በደቡብ ክልል ባለ ብዙ ገጽ ዕድገት እና ዘላቂ ሰላም እንዲኖር የአስተዳደራዊ መዋቅር መርሆውን ቅድሚያ ሰጥቶ መመልከት አስፈላጊ እንደ ሆነ ተስማምተናል” ብለዋል።
ይሄም ሀገሪቱ በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ እና ሌሎች ፖለቲካዊ ችግሮች ተወጥራ ባለችበት በዚህ ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለጉዳዩ ትልቅ ትኩረት መስጠታቸውን የሚያመለክት እንደሆነ በብዙዎች ይታመናል፡፡
የአደረጃጀት ጥያቄው አሁን የደረሰበት ደረጃ
80 አባላት ያሉት “የሰላም አምባሳደር” ኮሚቴ ከደቡብ ክልል ብሔሮች እና ብሔረሰቦች ተወካዮች ጋር በተለያዩ ጊዜያት ዉይይት ካደረገ በኋላ ክልሉን በማፍረስ ይፈጠር ስላለው አዲስ አደረጃጀት የመጨረሻ የውሳኔ ምክረ ሀሳብ ለጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅርቧል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ፣ የብልጽግና አመራሮች እና የፌደሬሽን ም/ቤት ተወካዮች ፣ በቀረበው የውሳኔ ሀሳብ ላይ ፣ ከክልሉ ዞኖች እና ከልዩ ወረዳ የፖለቲካ አመራሮች ጋር ሰኔ 2 ቀን 2012 ዓ.ም በጠቅላይ ሚኒስትር ጽ/ቤት ዉይይት አድርገዋል፡፡
ኮሚቴው ያቀረበው የአደረጃጀት የውሳኔ ሀሳብ የማህበረሰቡን ስነ ልቦና ፣ ቋንቋ ፣ መልክዓ ምድር (ጂኦግራፊ) እና የህዝቡን ዉሳኔ ታሳቢ ያደረገ እንደሆነ በውይይቱ ወቅት አስታውቋል፡፡
በዚህም መሰረት ነባሩ የደቡብ ክልል ፈርሶ በአራት ክልሎች እና በአንድ ልዩ ዞን እንዲደራጅ የቀረበው ዉሳኔ ተቀባይነት ማግኘቱን አል ዐይን አማርኛ በውይይቱ ከተሳተፉ ግለሰቦች ማረጋገጥ ችሏል፡፡
በዚህም መሠረት አዲስ እንዲመሰረቱ ከቀረቡት ተጠባቂ ክልሎች አንዱ ጋሞ፣ ጎፋ፣ ኮንሶ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ደራሼ፣ ቡርጂ፣ አማሮ ፣ ባስኬቶ እና ኮንሶ ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች በአንድ ክልል ማለትም “ኦሞቲክ ክልል” ተብለው እንዲደራጁ ፤ በደቡብ ክልል ማዕከላዊ እና ሰሜናዊ አቅጣጫ የሚገኙት ሀዲያ ፣ ከምባታ ጠምባሮ ፣ስልጤ፣ ጉራጌ ፣ የም እና ሀላባ አንድ ላይ እንዲደራጁ ፤ ቀድሞ በህዝበ ውሳኔ ጉዳዩን የጨረሰው የሲዳማ ዞን ብቻውን እንዲደራጅ ፤ ከፋ፣ቤንች ማጂ፣ ሸካ እና ዳውሮ በአንድ ክልል እንዲደራጁ ፤ ጌዴኦ ደግሞ በልዩ ዞን እንዲደራጅ የውሳኔ ሀሳብ ቀርቧል፡፡ ይሁንና ጌዴኦ ከየትኛው ክልል ጋር እንደሚሆን የተገለጸ ነገር ባለመኖሩ ወደፊት እልባት እንደሚያገኝ ይጠበቃል፡፡
የቀረበው የመጨረሻ የውሳኔ ምክረ ሀሳብ በአንድ ወር ዉስጥ ዉሳኔ እንዲያገኝ ለፌደሬሽን ምክር ቤት መመራቱንም አል ዐይን ያነጋገራቸው የውይይቱ ተሳታፊዎች ተናግረዋል፡፡
የውይይቱ ተሳታፊዎች ለአል ዐይን አማርኛ እንዳረጋገጡት በ”ኦሞቲክ” ስር እንዲደራጁ ሃሳብ የቀረበባቸው ዞኖች እና ወረዳዎች ጉዳይ አብዛኛውን ጊዜ ወስዶ ዉይይት የተደረገበት እና ከፍተኛ ክርክር ያስነሳ ጉዳይ ሆኗል፡፡ የወላይታ ዞን በዚህኛው የክልል አደረጃጀት ስር እንዲካተት በሀሳብ ደረጃ ቢቀርብም ፣ አደረጃጀቱ ዉስጥ ከሚገኙ ሌሎች ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች በተወከሉ ተሳታፊዎች ተቀባይነት ሳያገኝ መቅረቱንም ተናግረዋል፡፡ ግለሰቦቹ እንደሚሉት ወላይታ ዞን ብቻውን በክልል እንዲደራጅ የሚል ሀሳብ ነው አብዛኛው የውይይቱ ተሳታፊዎች ያቀረቡት፡፡
ከወላይታ ጋር በአንድነት መደራጀት እንደማይችሉ በዋናነት ሀሳባቸውን የገለጹት ከወላይታ ዞን ጋር ወሰን የሚጋሩት የጋሞ ፣ ጎፋ እና ዳውሮ ተወካዮች እንደሆኑም የውይይቱ ተሳታፊዎች ገልጸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ሰሞኑን ወደ ጋሞ ፣ ጎፋ እና ወላይታ ዞኖች በመሄድ ከሀገር ሽማግሌዎች ጋር ዉይይት እንደሚያደርጉ እና ዉይይቱን ተከትሎም የወላይታ ጉዳይ መፍትሔ እንደሚያገኝ ይጠበቃል፡፡ በመሆኑም ወላይታ ከሌሎች ጋር የማይደራጅ ከሆነ በተናጥል ክልል ሊመሰርት ይችላልም ነው የተባለው፡፡
“ከወላይታ ጋር አንደራጅም” በሚል የተለያዩ ዞኖች እና ልዩ ወረዳዎች ተወካዮች በውይይቱ ሀሳብ መሰንዘራቸውን ተከትሎ የወላይታ ዞን አስተዳደር “የጥላቻ ቅስቀሳ እየተደረገብኝ ነው” በሚል ዛሬ መግለጫ አውጥቷል፡፡
ዞኑ በመግለጫው “ሰሞኑን በተለያዩ ሚዲያዎች አንዳንድ ፀረ ህዝብ አመለካከት ያላቸው ቡድኖች እንዲሁም በከፍተኛ የመንግስት መዋቅር ውስጥ የሚገኙ ግለሰቦች በተራጀ ሁኔታ የተከበረውን የወላይታ ህዝብ የማይመጥን የጥላቻ ንግግር እንዲሁም ያለንበትን ዓለምአቀፋዊና ሀገራዊ ዕድገትና አስተሳሰብ ደረጃ የማይመጥን ኋላ ቀር አካሄድ እና የጥላቻ ዘመቻ የዞኑ መንግስት በፅኑ ያወግዛል” ብሏል፡፡
“ኦሞቲክ”ን በተመለከተ ለተፈጠረው አለመግባባት ዋነኛው ምክንያት ከዚህ ቀደም በተለያዩ ጊዜያት በነበሩ የአስተዳደር መዋቅሮች ወቅት የነበሩ የቆዩ ቁርሾዎች መሆናቸው የተገለጸ ሲሆን ፣ የቀድሞው ሰሜን ኦሞ ዞን ሲበተን የተፈጠሩ አለመግባባቶችን ደግሞ አስተያየት ሰጪዎቹ በማሳያነት ያነሳሉ፡፡ የክልል ማዕከልነት ጉዳይም ሌላኛው ያለመግባባት ምንጭ እንደሆነ ተጠቅሷል፡፡
ከ“ኦሞቲክ” ጋር ይደራጃል የተባለው ኮንታ በ“ኦሞቲክ” ዉስጥ ይሆናሉ ተብለው ከሚጠበቁት ዉስጥ ከማናቸውም ጋር በወሰን የማይገናኝ መሆኑም ጥያቄ ያስነሳ ጉዳይ ነበር ተብሏል፡፡ ለዚህ ምክንያት የሆነው ዳውሮ ከከፋ ፣ቤንች ማጂ እና ሸካ ጋር ለመደራጀት በመወሰኑ ነው፡፡
የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዛሬ ሰኔ 3 ቀን 2012 ዓ.ም ባካሔደው 5ኛ ዓመት የሥራ ጊዜ 2ኛ መደበኛ ስብሰባ በደቡብ ክልል የክልልነት ጥያቄ ላይ ዉሳኔ አሳልፏል፡፡
የክልልነት ጥያቄዎችን በተገቢው መንገድ ለማስተናገድ የጋራ መድረኮችን የማመቻቸት፣ የምክር ቤቱን አስፈጻሚ ከክልሎች አስፈጻሚዎች ጋር የማገናኘትና የማወያየት፣ ከዚህ ቀደም የተጠኑ ጥናቶችንና የሰላም አምባሳደሮችን ስራ እንዲሁም ሕዝብን በማወያየት የመጨረሻ ውሳኔ ለማሳለፍ የሚያስችል የውሳኔ ሃሳብ የሕገ መንግሥት ትርጉምና የማንነት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ይዞ እንዲቀርብ በምክር ቤቱ በአብላጫ ድምጽ ተወስኗል።