ኢትዮጵያ ለአየር ንብረት ለውጥ በሚቀጥሉት 30 ዓመታት 34 ቢሊዮን ዶላር ከሀገር ውስጥ አሰባስባለሁ አለች
ኢትዮጵያ በኬንያ እየተካሄደ ባለው የመጀመሪያው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ እየተሳተፈች ነው
ሀገሪቱ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እስከ 2050 ድረስ 170 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋታል ተብሏል
ኢትዮጵያ በኬንያ እየተካሄደ ባለው የመጀመሪያው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ላይ እየተሳተፈች ነው።
ሀገሪቱ የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም እስከ 2050 ድረስ 170 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልጋታል ተብሏል።
ኢትዮጵያ በሚቀጥሉት 30 ዓመታት ልማቷን ትመራበታለች የተባለና የአየር ንብረት ለውጥን ያማከለ እቅዷን በሀምሌ ወር ይፋ አድርጋለች።
የ2015ቱን የፓሪስ ስምምነት መነሻ አድርጎ ተነድፏል የተባለው የኢትዮጵያ ዳጎስ ያለ እቅድ “የረጅም ዓመት ዝቅተኛ ልቀትና የአየር ንብረት ተቋቋሚ የልማት ስትራቴጂ” ይሰኛል።
በዚህ እቅድ ሀገሪቱ ትርፍና ኪሳራዋን አስልታ መከላከልና መቋቋም የሚያስችል “የአየር ንብረት ፋይናንስ” በሚቀጥሉት 30 ዓመታት 170 ቢሊዮን ዶላር ያስፈልገኛል ብላለች።
ከእዚህም ውስጥ 20 በመቶው (1.9 ትሪሊዮን ብር ገደማ) በሀገሪቱ አቅም (ፐብሊክ ፋይናንስ) እንደሚሸፈን እቅዱን የነደፈው የፕላንና ልማት ሚንስትር ፍጹም አሰፋ (ዶ/ር) በናይሮቢ ኬንያ እየተካሄደ በሚገኘው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ነግረውናል።
በዓለም አቀፍ የአየር ንብረት ለውጥ ገንዘብ አመዳደብ ክርክር እያስነሳ ሲሆን፤ በተለይም ከፍተኛ ልቀት ያለባቸው ምዕራባዊያን ሀገራት በአየር ንብረት ለውጥ ጉዳት እየደረሰባቸው ላሉ እንደ አፍሪካ ያሉ አህጉራት ገንዘብ ማቅረብ እንዳለባቸው ይታመናልም።
በአየር ንብረት ለውጥ ላይ የሚያተኩረው የዘንድሮው ኮፕ28 ሰብሰባ በአረብ ኢምሬትስ አስተናጋጅነት ይካሄዳል። ሰብሰባው በፖሪሱ ስብሰባ ስምምነቱ ላይ የተደረሰባቸው ሀሳቦች ተግባራዊ በሚሆኑበት ጉዳይ ላይ እንደሚመክር ይጠበቃል።