የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ የጋራ አቋም የሆነው “የናይሮቢ ስምምነት” ጸደቀ
የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ በየሁለት ዓመቱ እንዲካሄድ ተወስኗል
ስምምነት ሀገራት ከልማትና ከአየር ንብረት ለውጥ እርምጃ መምረጥ ሊገደድ አይገባም ብሏል
የአፍሪካ መሪዎች ለመጀመሪያ ጊዜ በተካሄደው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ በዓለም ሀገራት ወኪሎች፣ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች፣ የልማት አጋሮችና ለሌሎችም ተሳታፊዎች ፊት “የናይሮቢ ስምምነት”ን (ናይሮቢ ዲክላሬሽን) በሙሉ ድምጽ ተቀብለዋል።
መሪዎቹ በዝግ ከተወያዩ በኋላ ይፋ ያደረጉት ስምምነት፤ አፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥን በመቋቋም እንድታድግ የሚወተውት ነው።
የእርምጃ ጥሪ በተሰኘው የአፍሪካ የአቋም ማሳወቂያ፤ ማበረታቻ፣ እውቅና፣ ውትወታና የትኩረት አቅጣጫዎች ተለይተው ተንጸባርቀዋል።
የአህጉሪቱ የህዝብ ቁጥር እድገትና ሌሎችንም አቅሞች እውቅና እዲሰጣቸው የጠየቀም ሲሆን፤ አፍሪካ ለአየር ንብረት ለውጥ ተጠቂ ብቻ ሳይሆን መፍትሄ መሆን ትችላለችም ብሏል።
የአፍሪካ ህብረት አጀንዳ 2030 ሊጠናቀቅ ሰባት ዓመታት ብቻ ቀርተውታል ያለው የስምምነቱ ሰነዱ፤ 600 ሚሊዮን አፍሪካዊያን የኤሌክትሪካ አገልግሎት እንደማያገኙና 970 ሚሊዮኑ ደግሞ ንጹህ የምግብ ማብሰያ የላቸውም ተብሏል።
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በፍጥነት ልቀትን እንዲቀንስ፣ ኃላፊነቱን እንዲወጣ፣ ቃሉን እንዲያከብር እንዲሁም የአህጉሪቱን የአየር ንብረት ለውጥ ፍልሚያ እንዲያግዝ ተጠይቋል።
በ2050 የአፍሪካ ሀገራት የተረጋጋ መካከለኛ ኢኮኖሚ እንዲኖራቸውም ከከባቢ ጋር የተስማማ ኢንቨስትመት ያስፈልጋል ብሏል።
ለዓለም ለልማትና ለአየር ንብረት እርምጃዎች የሚሆኑ የገንዘብ ማሰባሰብ ላይ ተጨማሪ ስራዎች ይጠበቃሉ በማለት፤ የትኛውም ሀገር ከልማትና ከአየር ንብረት ለውጥ እርምጃ መምረጥ ሊገደድ አይገባም በማለት አስምሯል።
የንግድ ልውውጥ ላይ ከባቢን የተመለከቱ ቀረጦች የአንድ ወገን፣ አግላይና የዘፈቀደ ሳይሆኑ የባለ ብዙ ወገን መሆን አለባቸው በማለት ማስተካከያ ይደረግ ብሏል።
የካርቦን ታክስ በተለይም በነዳጅ፣ አቪየሽንና የውሃ ትራንስፖርት ላይ እንዲጣል የዓለም መሪዎች በናይሮቢ ስምምነት ተጠይቀዋል።
የፋይናንስ ስርዓቱ ለአፍሪካ በሚሆን መልኩ መሰራት አለበት በማለትም የብድርና የእፎይታ ጉዳዮች እንዲጤኑ ሀሳብ አቅርቧል።