የአፍሪካ የአየር ንብረት ለውጥ በናይሮቢ ስምምነት (ናይሮቢ ዲክላሬሽን) ተጠናቀቀ
የናይሮቢ ስምምነት የአፍሪካ ሀገራትን ለመርዳት የፋይናንስ ስርዓቱ ላይ ማሻሻያ እንዲደረግም ጠይቋል
የናይሮቢ ስምምነት በህዳር ለሚካሄደው የኮፕ28 ጉባኤ ለአፍሪካ ድርድር አቋም ሆኖ ይቀርባል
የመጀመሪያው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ ረቡዕ ሲጠናቀቅ ለአየር ንብረት ለውጥ እርምጃዎች የዓለም መሪዎች ፈንድና ታክስን እንዲደግፉ ጥሪ ቀርቧል።
የናይሮቢ ስምምነት የአፍሪካ ሀገራትን ለመርዳት የፋይናንስ ስርዓቱ ላይ ማሻሻያ እንዲደረግም ጠይቋል።
ትልቅ ምዕራፍ የሆነው የአፍሪካ የአየር ንብረት ጉባኤ አህጉሪቱ ለአረንጎዴ ኃይድሮጂን ያላትን እምቅ ሀብት በማጉላትና የካርቦን ታክስ ድጋፍን በመጠየቅ በናይሮቢ ስምምነት ተጠናቋል።
"ይህ ስምምነት በዓለም የአየር ንብረት ለውጥ ንግግር ለአፍሪካ የጋራ አቋም መሠረት ሆኖ ያገለግላል" ሲል የስምምነት ሰነዱ ያትታል።
አክሎም "የትኛውም ሀገር ከአየር ንብረት ለውጥ እርምጃና ከልማት ለመምረጥ መገደድ የለበትም" ብሏል።
በ1.3 ቢሊዮን የህዝብ ቁጥር ባለው የአህጉሪቱ መሪዎች የተደገፈው ስምምነት፤ በህዳር ለሚካሄደው የኮፕ28 ጉባኤ ለአፍሪካ ድርድር አቋም ሆኖ ይቀርባል።
ዓለም አቀፍ የካርቦን ታክስ እንዲጣል የወተወተው ለሦስት ቀናት የዘለቀው ጉባኤ፤ ግዙፍ ልቀት ያለባቸው ሀገራት ታክስ እንዲከፍሉና ሀብታም ሀገራት ቃል የገቡትን የ100 ቢሊዮን ዶላር ገንዘብ እንዲለቁ ጥሪ አቅርቧል።
የናይሮቢ ስምምነት በነዳጅ፣ አቪየሺንና አየር ትራንስፖርት ላይ የካርቦን ታክስ እንዲጣል የዓለም መሪዎች ይደግፉ ብሏል።