መንግስት የአለም አቀፉ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ባወጣው መግለጫ መበሳጨቱን ገለጸ
መንግስት ኮሚሽኑ ከስልጣኑ ውጭ የጸጥታው ምክርቤት በኢትዮጵያ ላይ እርምጀ እንዲወሰድ ጥሪ ማድረጉን ተቃውሟል
የኮሚሽኑ ባለሙያዎች የተመድ የጸጥታው ም/ቤት በኢትዮጵያ ጉዳይ እንዲሰበሰብ ጥሪ ማድረጋቸው የኢትዮጵያን መንግስት አበሳጭቷል
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ባወጣው መግለጫ የአለምአቀፍ የሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን ባለሙያዎች ከትናንት በስትያ ባወጡት መግለጫ መበሳጨቱን ገልጿል፡፡
በኢትዮጵያ በተፈጠረው ጦርነት የተፈጸሙ የሰብአዊ መብት ጥሰቶችን እንዲመረምር በተመድ ኃላፊነት የተሰጠው የባለሙያዎች ቡድን የኢትዮጵያ ችግር የሰላም እና የደህንነት ስጋት ስለሆነ የተመድ የጸጥታው ምክርቤት እርምጃ ይውሰድ የሚል ይዘት ያለው መግለጫ አውጥተው ነበር፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሩ ጦርነቱ በህወሓት መጀመሩን ደፍሮ ያልገለጸ ኮሚሽን ጉዳዮች የሰላም እና የጸጥታ ስጋት ናቸው ብሎ ማስተጋባት አይችልም ብሏል፡፡
ኮሚሽኑ ከስልጣኑ ውጭ የጸጥታው ምክርቤት በኢትዮጵያ ላይ እርምጀ እንዲወሰድ ጥሪ ማድረጉ፣ኮሚሽኑ የተቋቋመበት እና ስራው ፖለቲካዊ አላማ አለው የሚለውን የኢትዮጵያ መንግስት ግምገማ የሚያረጋግጥ ነው ብሏል የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር፡፡
ሚኒስቴሩ የሰብአዊ መብት ጉዳዮችን ጫና ለማድረግ እየተጠቀመባቸው ነው፤ ከመንግስት ጋር ሊኖር የሚችለው ትብብር እየዘጋ ነው ብሏል፡፡
በፌደራል መንግስት እና በሽብርተኝነት በተፈረጀው ህወሓት መካከል የነበረው ግጭት ለወራት ጋብ ብሎ የነበረ ቢሆንም ባለፈው ሳምንት በድጋሚ ተቀስቅሷል።
የፌደራል መንግስት ህወሓት የሰላም አማራጭን ወደ ጎን በመተው ጥቃት መሰንዘሩን ገልጾ ከቆቦ ከተማ የከተማ ውጊያ ላለማድረግ ማፈግፈጉን መግለጹ ይታወሳል።
መንግስት የህወሓትን ጥቃት እየመከተ እንደሚገኝም እየገለጸ ነው።
በአማራ ክልል በሰቆጣ፣በወልዲያ፣ በደሴ እና በከምቦልቻ ከጦርነቱ ጋር በተያያዘ ሰጋት የሰአት እለፊ ገደብ መጣሉ ይታወሳል።
የፌደራል መንግስት እና ህወሓት አካለት ለወራት የዘለቀውን የተናጠል ተኩስ አቁም በመጣስ አንደኛው ሌላኛውን በመወንጀል ላይ ናቸው።