ህወሓት እና ኤርትራ ወደ ጠቅላላ ጦርነት ከገቡ የኢትዮጵያ መንግስት ምላሽ ምን ሊሆን ይችላል?
እንዲህ ዐይነት ጉዳዮች ሊዳኙ የሚችሉበት ዓለም አቀፍ ህግ እንደሌለ የሚናገሩት ሌላኛው ምሁር ደግሞ አዲስ ዓለም አቀፋዊ ክፍተት ሊሆን ይችላል ብለዋል
ምዕራባውያን በኢትዮጵያ ላይ የያዙት አቋም መሻሻል ማሳየቱን የሚናገሩት ምሁሩ የፌዴራሉ መንግስት ምናልባትም ከህወሓት ጎን ሊቆም እንደሚችል ተናግረዋል
ህወሓት ጥቅምት 24 ቀን 2012 ዓ.ም በሀገር መከላከያ ሰራዊት የሰሜን እዝ ላይ ጥቃት መክፈቱን ተከትሎ ነበር በኢትዮጵያ ጦርነት የተጀመረው፡፡
በድንገት በመጠቃቱ ወደ ድንበሯ የገባውን የኢትዮጵያን ጦር ያስጠጋችው ኤርትራም በዚህን ጊዜ ነበር ለደህንነቴ ያሰጋኛል በሚል ጦሯን ወደ ኢትዮጵያ ያስገባችው፡፡
የሀገር መከላከያ ሰራዊት በጥቂት ወራት ውስጥ ትግራይን መልሶ ቢቆጣጠርም ከሰኔ 2013 ዓ.ም ጀምሮ ክልሉን ለቆ ወደ አማራ እና አፋር አዋሳኝ አካባቢዎች አፈግፍጎ እንደነበር ይታወሳል፡፡
ይሁንና ህወሓት ወደ አፋር እና አማራ ክልሎች ጥቃት ከፍቶ በርካታ ዞኖችን ተቆጣጥሮ ቆይቶ በተደረገበት የመልሶ ማጥቃት እርምጃ ከተወሰኑ ወረዳዎች በስተቀር ወደ ትግራይ ክልል ተመልሷል፡፡
የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ከተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጋር በጋራ እና በተናጥል በተደረጉ ጥናቶች በጦርነቱ የተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ምርመራ ሪፖርቶች በተለያዩ ጊዜያት ይፋ ሆነዋል፡፡
በነዚህ የምርመራ ሪፖርቶች ግኝት መሰረት የኤርትራ ጦርን ጨምሮ በሁሉም የጦርነቱ ተሳታፊ ሀይሎች የጦርነቱ ተሳታፊ ያልሆኑ ንጹሃን ተገድለዋል፣ አስገድዶ ደፈራዎች ተፈጽመዋል እንዲሁም መሰረተ ልማቶች ወድመዋል፡፡
የኤርትራ መንግስት ጦሩ በምርመራ ሪፖርቱ እንደፈጸማቸው የተጠቀሱ ጥሰቶችን እንዳልፈጸመ በማስታወቅ ውድቅ ማድረጉ አይዘነጋም፡፡
ይሄንን ተከትሎ የኤርትራ ጦር በትግራይ ክልል የተለያዩ ወንጀሎችን ፈጽሟል በሚል በተደጋጋሚ ህወሓት ክሶችን ሲያሰማ የቆየ ሲሆን የኤርትራ መንግስት በበኩሉ ክሱን ውድቅ ሲያደርግ ይሰማል፡፡
ከሰሞኑ ኤርትራ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴሯ በኩል ህወሓት ኤርትራን ለመውረር ዝግጅት እያደረገ ነው የሚል መግለጫ አውጥታለች፡፡
የሁለቱ ወገኖች መካረር እየጨመረ የመጣ ሲሆን ወደ ይፋዊ ጦርነት ይገቡ ይሆን? የሚል ስጋትም እያየለ መጥቷል፡፡
የኢትዮጵያ አንድ አካል የሖነችው ትግራይ ክልልን እያስተዳደረ ያለው እና በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት በአሸባሪነት የተፈረጀው ህወሓት ከኤርትራ ጋር አጠቃላይ ጦርነት ከጀመረ ጉዳዩ ወዴት ሊመራ ይችላል? የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስትስ ለዚህ ጉዳይ እንዴት ምላሽ ሊሰጥ ይችላል? ሲል አል ዐይን አማርኛ የዓለም አቀፍ ህግ ምሁራንን ጠይቋል፡፡
ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ያላት ግንኙነት በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ ገለጸች
በጅግጅጋ ዩንቨርሲቲ የሕግ መምህሩ ሰለሞን ጓዴ በህወሓት መራሹ የኢህአዴግ የአስተዳደር ዘመን ጀምሮ ሁለቱ ወገኖች ግንኙነታቸው የተበላሸ እንደነበር በመጥቀስ ከጥቅምት 24 ጀምሮ ደግሞ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪም ጦርነት ውስጥ ነበሩ ብለዋል፡፡
ህወሓት አገር ለመሆን እየተለማመደ ነው ያሉት መምህር ሰለሞን “በኔ እምነት ሁለቱ አካላት ጦርነት ከጀመሩ ቆይተዋል፡፡ አጠቃላይ ጦርነትም መጀመራቸው አይቀርም” ሲሉም አክለዋል፡፡
ህወሓት የኤርትራ መንግስት ስጋቴ ነው ብሎ ያምናል፤ ኤርትራም ህወሓት ስጋቷ መሆኑን በተደጋጋሚ በምታወጣቸው መግለጫዎች ገልጻለች ሲሉም መምህር ሰለሞን ገልጸዋል፡፡
ህወሓት መከላከያን በድንገት በማጥቃቱ የኢትዮጵያ መንግስት የኤርትራን መንግስት ጋብዞ ወደ ኢትዮጵያ ገብቶ ጦሩ ከህወሓት ሲዋጋ ነበር የሚሉት መምህር ሰለሞን ይህ ውሳኔ ኢትዮጵያን እና ኤርትራን በዓለም አቀፉ ማህበረሰብ ዘንድ ሲያስወቅሳቸው እንደነበርም አንስተዋል፡፡
እንደ መምህር ሰለሞን ገለጻ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን የኤርትራ እና ኢትዮጵያ መንግስት ግንኙነት በመሻከር ላይ ሲሆን በጦርነቱ ምክንያት ጫና ውስጥ ገብቶ የነበረው የኢትዮጵያ መንግስት አሁን ላይ መሻሻል አሳይቷል፡፡
አሜሪካ፣ የአውሮፓ ህብረት እና ሌሎች ዓለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማት በኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት ላይ ጫናቸውን እየቀነሱ መጥተው አሁን ላይ በጥሩ መሻሻል ላይ ናቸው ሲሉም አክለዋል፡፡
ምዕራባውያን አቋማቸውን በኢትዮጵያ ላይ ለምን መሻሻል እንዳሳዩ እና በምትኩ የኢትዮጵያ መንግስት ምን እንደሰጠ ግልጽ አይደለም የሚሉት መምህር ሰለሞን በተቃራኒው ምዕራባውያን ሀገራት በኤርትራ ላይ ጫናቸው እንዳየለ ይናገራሉ፡፡
በዚህ መካከል ህወሓት ከኤርትራ ጋር ይፋዊ ጦርነት ከጀመረ የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት ምላሽ የሚወሰነው በጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ (ዶ/ር) የሚመራው የፌደራል መንግስት እና ህወሓት እያደረጉት ባለው ድርድርና በምዕራባውያን ሀገራት ፍላጎት እንደሆነም አስቀምጠዋል፡፡
በተጨማሪም የፌደራል መንግስት በህዝብ የተነሳውን የወልቃይትን የማንነት ጥያቄዎች ህጋዊ ምላሽ ለመስጠት "ዳተኛ" መሆኑ እና በአማራ ክልል የተለያዩ ምክንያቶችን መነሻ በማድረግ የሚደረጉ ውክቢያዎችን ስንመለከት ህወሓት እና ኤርትራ ወደ ለየለት ጦርነት ከገቡ የፌደራል መንግስት ውግንናው ለህወሓት ሊሆን እንደሚችል ይገመታል ሲሉም አክለዋል መምህር ሰለሞን፡፡
የኢትዮጵያ ፌደራል መንግስት ህወሓት እና ኤርትራ ወደ አጠቃላይ ጦርነት ቢያመሩ እና ጉዳዩን በዓለም አቀፍ ህግ መሰረት ምላሽ ልስጥ ቢል ህጉ ምን ይላል? በሚል ለመምህር ሰለሞን ላነሳንላቸው ጥያቄ ተከታዩን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡
“ዓለም አቀፍ ህጎች የሀያላን ሀገራት ፍላጎት ማስፈጸሚያዎች እንዲሆኑ ተደርገው የተዘጋጁ ናቸው፣ የህወሓት እና ኤርትራ ጦርነት ጉዳይም በዓለም አቀፍ ህግ ስምምነቶች መሰረት የሚፈታ አይደለም” ብለዋል፡፡
“ይህን ጉዳይ የሚወስኑት ሀገራት እና ቡድኖች ከጀርባ የሚያደርጓቸው ስምምነቶች ናቸው” ሲሉም ነው የተናገሩት፡፡
ሌላኛው የዓለም አቀፍ ህግ ጠበቃ ፋሲል ስለሺ በበኩላቸው የህወሓት እና ኤርትራ ጉዳይ ሁለቱ በተለያየ ቁመና ላይ ያሉ በመሆኑ ሁለቱ አካላት ወደ ጦርነት ቢያመሩ ጉዳዩ በዓለም አቀፍ ህግ አይዳኝም ይላሉ፡፡
“ኤርትራ ሉዓላዊ ሀገር ናት፤ ህወሓት ደግሞ በኢትዮጵያ ካሉ 10 ክልሎች መካከል አንዱ ነው በመሆኑ የሁለቱን አካላት ጉዳይ በዚህ ነው የሚዳኙት ብሎ ለመናገር አይቻልም“ ሲሉም አክለዋል፡፡
“በዓለም ላይ እስካሁን የአንድ ሀገር ክልል በሌላ ሉዓላዊ ሀገር ላይ ጦርነት የከፈተ አካል አላውቅም” ያሉት የሕግ ባለሙያው ጠበቃ ፋሲል ይህ ከሆነ ለዓለም አዲስ ክስተት ሊሆን ይችላል ብለዋል፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የመስሪያ ቤታቸውን የዘጠኝ ወር የሥራ ክንውን ሪፖርት ባሳለፍነው ሰኞ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ሲያቀርቡ ኢትዮጵያ ከኤርትራ ጋር ያላት ግንኙነት በመልካም ሁኔታ ላይ እንደሚገኝ አስቀምጠዋል፡፡
ኤርትራ እና ኢትዮጵያ የጋራ ጥቅሞቻቸውን መሰረት በማድረግ ግንኙነታቸውን ይበልጥ ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑንም ነው አቶ ደመቀ ለምክር ቤቱ የተናገሩት፡፡
በዚህም መሰረት የድንበር አካባቢና የሰዎች ዝውውርን የሚያሳልጡ የመሰረተ ልማት ግንባታዎች፣ የወደብ አጠቃቀም የንግድ ልውውጥ፣ የጉምሩክ፣ የኢሚግሬሽንና የመሳሰሉ የሁለቱን ሀገሮች ሕዝብ ተጠቃሚ ሊያደርጉ የሚችሉ የትብብር ማዕቀፎችን ለማበጀት እየተሰራ ይገኛል ብለዋል፡፡