አሜሪካ ከሩሲያ ጋር የገባቻቸውን ሁለት የጦር መሳርያ ስምምነቶችን እንደጣሰች ሞስኮ ገልጻለች
ሩሲያ ከአሜሪካ ጋር ቀጥታ ጦርነት ልትጀምር እንደምትችል አስጠነቀቀች።
አሜሪካ እና ሩሲያ የረጅም ጊዜ ባላንጣነት ታሪክ ያላቸው ሲሆን ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃልኪዳን ድርጅት( ኔቶን) እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ከሩሲያ ጋር ቀጥታ ጦርነት መጀመሩ ደግሞ ግንኙነታቸው በመበላሸት ላይ ይገኛል።
በአሜሪካ የሩሲያ አምባሳደር ሩሲያ እና አሜሪካ ወደ ቀጥታ ጦርነት ሊገቡ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል።
እንደ ሩሲያ ቱዴይ ዘገባ ከሆነ አሜሪካ ከሩሲያ ጋር ያላትን ግንኙነት የያዘችበት መንገድ ሀላፊነት የጎደለው፣ ለጦርነት ጥቂት ነገሮች የቀሩበት ደረጃ ላይ መድረሱን አምባሳደሩ ተናግረዋል።
አሁን ላይ የሩሲያ እና አሜሪካ ግንኙነት የማይገመት ደረጃ ላይ መድረሱን የሚናገሩት አምባሳደሩ የኑክሌር ጦርነት ሊጀምሩ እንደሚችሉም ስጋታቸውን ጠቁመዋል።
ሩሲያ እና አሜሪካ ከዚህ በፊት የደረሱባቸውን ሁለት የጦር መሳሪያ ለሌላ ሀገር ያለማስታጠቅ ስምምነቶች በአሜሪካ መጣሳቸውንም አምባሳደሩ ገልጸዋል።
በመሆኑም ሁለቱ የዓለማችን ሀያላን ሀገራት ወደለየለት ጦርነት እንዳያመሩ የተሰጋ ሲሆን በቀጣም ምን ሊፈጠር እንደሚችል አልታወቀም።
ዩክሬን ከሩሲያ እየደረሰባት ያለውን ጥቃት ለመመከት ዘመናዊ የጦር መሳሪያ እየለገሰች ያለችው አሜሪካ በሩሲያ በኩል እየቀረቡ ስላሉ ሀሳቦች ዙርያ እስካሁን በይፋ ያለችው ነገር የለም።
አሜሪካ ሩሲያ የዩክሬን ዛፖሮዚዬ የኑክሌር ጣቢያን መያዟ ትክክል አለመሆኑን የገለጸች ሲሆን ሩሲያ በበኩሏ የኑክሌር ጣቢያውን ተመድ እንዲቆጣጠረው ምክረ ሀሳብ አቅርባለች።
የሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ከተጀመረ 174ኛ ቀኑ ላይ ሲሆን እስካሁን ባሉት ጊዜያት ውስጥ ከ10 ሚሊዮን በላይ ዩክሬናዊያን ወደ ጎረቤት ሀገራት ተሰደዋል።
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዶሚር ዘለንስኪ በየዕለቱ 200 ወታደሮቻቸው እየተገደሉባቸው እንደሆነ መናገራቸው ይታወሳል።