የፌደራል መንግስትና ህወሓት ባወጡት መግልጫ ጦርነት መጀመሩን አስታወቁ
የፌደራል መንግስትና ህወሓት ግጭቱን በድርድር ለመፍታት ያላቸውን ፍላጎት በተናጠል ሲገልጹ ቆይተዋል
መንግስት እና ህወሓት ተኩስ አቁሙን በመጣስ እየተወነጃጀሉ ነው
የፌደራል መንግስት እና ህወሓት ለወራት ቆሞ የነበረውጦርነት መጀመሩን ባወጡት መግለጫ አስታውቀዋል።
ህወሓት ዛሬ ባወጣው መግለጫ መከላከያ ሰራዊትና እና የአማራ ክልል ልዩ ኃይል በትግራይ ደቡባዊ አቅጣጫ ባለው ግንባር በኩል ተኩስ መክፈታቸውን አስታውቋል፡፡
የህወሓት መግለጫን ተከትሎ የፌደራል መንግስት ባወጣው መግለጫ የህወሓት ኃይሎች በዛሬው እለት ጠዋት 11 ሰዓት በተለያየ አቅጣጫ ጥቃት መፈጸማቸውን ገልጿል፡፡
ህወሓት በመግለጫው እንደተከፈተበት የገለጸው ጥቃት ዋና አላማም “ከምእራብ ትግራይ እና ምእራብ ጎንደር በኩል ወደ አዲያቦ፣ አስገደ እና ጸለምት” ጥቃት ለማድረስ ነው ብሏል፡፡ “ጠላት” በትግራይ ህዝብ ላይ ከበባ በማድረግ ግፍ ፈጽሟል ያለው ህወሓት አሁን ላይ ለወራት የቆየውን ተኩስ አቁም ጥሷል ሲል መንግስትን ከሷል፡፡
የፌደራል መንግስት ክሱን እንዳማይቀበልና ትንኮሳውንም ህወሓት እንደጀመረው በመግለጫው አስታውቋል፡፡
መንግስት በመግለጫው ህወሓት የሰላም አማራጮችን ወደ ጎን በበተው “ከበባውን እንሰብራለን፣ መተማመኛችን ክንዳችን ነው፣ የትግራይ መሬቶች ተወረዋል፣ እናስለቅቃለን፣ ወዘተ በሚል ፉከራ ታጅበው ባለፉት ስድስት ወራት የተለያዩ ትንኮሳዎችን ሲያደርጉ ቆይተዋል” ብሏል ።
ህወሓት በምእራብ ግንባር በኩል ሙከራ ማድረጉን እና ሙከራው እንደከሸፈበትም የገለጸው መንግስት ህወሓት ዛሬ በከፈተው ጥቃት “ተኩስ ማቆሙን በይፋ አፍርሷል” ብሏል
የፌደራል መንግስት በሽብርተኝነት ከፈረጀው ህወሓት ጋር ያለውን ግጭት በድርድር ለመፍታት ማስታወቁ፤ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንደሚደረደር መግለጹ ይታወሳል፡፡
ህወሓትም በተመሳሳይ ለድርድር ዝግጁ መሆኑን ገልጾ ነበር፡፡
ድርድሩ በአሪፍካ ህብረት መሪነት እየተካሄደ ቢሆንም ህወሓት በአፍሪካ ህብረት ላይ እምነት እንደሌላው መግለጹ ይታወሳል፡፡