ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከዩኤኢ አቻቸው ጋር በስልክ ተወያይተዋል
የኢትዮጵያ መንግስት የሀውሲ አማጺያን ለአካባቢው ሰላም አስጊ ናቸው አለ፡፡
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከዩኤኢ ውጭ ጉዳይ እና ዓለም አቀፍ ትትብር ሚኒስትር ሼክ አብዱላህ ቢን ዛይድ አል ናሕያን ጋር በስልክ ተወያይተዋል፡፡
ሚኒስትሩ በዚህ ጊዜ እንዳሉት የሀውሲ ታጣቂዎች በዩኤኢ ሲቪሊያን በሚንቀሳቀሱባቸው አካባቢዎች እና ተቋማት ላይ የተፈጸሙ የሽብር ጥቃቶችን አውግዘዋል፡፡
ክስተቱ ለአካባቢው ሀገገራት ሰላም አስጊ መሆኑን የተናገሩት አቶ ደመቀ ኢትዮጵያ የተባበሩት ዓረብ ኢምሬት ሉዓላዊነቷን ለማስጠበቅ በግዛቷ ከምትወስዳቸው እርምጃዎች ጎን እንደምትቆምም ተናግረዋል፡፡
የሓውሲ አማጺያን ጥቃት ዓለም አቀፍ ህጎችን የሚጥስ እና ለአካባቢው አገራት ሰላም ጸር መሆኑንም በስልክ ውይይቱ ወቅት መነገራቸው ተገልጿል፡፡
የሀውሲ አማጺያን ባሳለፍነው ሳምንት በዩኤኢ ላይ በፈጸሙት የባሊስቲክ ሚሳኤል ጥቃት ሶስት ሰዎች ሲሞቱ ስድስት ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸው ይታወሳል፡፡ይህ የሽብር ቡድን በያዝነው ሳምንት ተመሳሳይ ጥቃት ፈጽሞ በዩኤኢ መከላከያ ሀይል መምከኑም አይዘነጋም፡፡