ሪያድ በስምምነት ሃሳቡ መሰረት የሃገሪቱ መንግስት እና የሃውቲ አማጽያን መደራደር እንደሚጀምሩ አስታውቃለች
ሳዑዲ አረቢያ በየመን በመካሄድ ላይ ያለውን የእርስ በእርስ ጦርነት ለማብቃት የሚያስችል የስምምነት ሃሳብ አቀረበች፡፡
የስምምነት ሃሳቡ በመላ ሃገሪቱ ተኩስ ለማቆም ጭምር የሚያስችል እንደሆነ የሳዑዲ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ልዑል ፈይሰል ቢን ፈርሃን አስታውቀዋል፡፡
ልዑል ፈይሰል ዓለም አቀፍ እውቅና ያለው የሃገሪቱ መንግስት እና በኢራን እንደሚደገፉ የሚነገርላቸው የሃውቲ አማጽያን በስምምነት ሃሳቡ መሰረት መደራደር እንደሚጀምሩም ነው ያስታወቁት፡፡
ለስምምነቱ ተፈጻሚነት እንሰራለንም ብለዋል ውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ፡፡
ሃገሪቱ የገባችበትን የእርስ በርስ ጦርነት ለማስቆም ፖለቲካዊ መፍትሔዎችን ማበጀቱ እንደሚጠቅምም ልዑሉ ገልጸዋል፡፡
ሁለቱ አካላት ለመስማማት የሚችሉም ከሆነ ምግብና ነዳጅን የመሳሰሉ ቁሳቁሶች የሚገቡ የሚወጡባቸው የሰንዓ እና የሆዴይዳ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያዎች ዳግም እንደሚከፈቱም ነው የተናገሩት፡፡
ሆኖም የኢራንን ጣልቃ ገብነት ተቃውመዋል፡፡ ቴህራን ለአማጽያኑ የምታደርገውን የጦር መሳሪያ አቅርቦት ጭምርም ነው የተቃወሙት፡፡
አማጽያኑ ጦርነቱን ለማብቃት የስምምነት ሃሳቡን እንዲቀበሉም ነው ልዑል ፈይሰል ጥሪ ያቀረቡት፡፡
ልክ ሃውቲዎች መስማማታቸውን ከሚገልጹበት ጊዜ ጀምሮ ወደ ተግባር እንደሚገባም ጠቁመዋል፡፡