ኢትዮጵያውያኑ በዓለም አቀፉ የስደተኞች ተቋም ድጋፍ ነው ወደ ሃገራቸው የተመለሱት
የእርስበርስ ጦርነት ባደቀቃት የመን ለችግር ተጋልጠው የነበሩ 140 ኢትዮጵያውያን ወደ ሃገራቸው ተመለሱ፡፡
ኢትዮጵያውያኑ በዓለም አቀፉ የስደተኞች ተቋም ድጋፍ ነው ከየመን አደን ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ ተነስተው ዛሬ አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ የደረሱት፡፡
ተቋሙ የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከተከሰተ በኋላ በሁለቱ ሃገራት መካከል ያስተባበረው የመጀመሪያው ሰብዓዊ ምላሽ/በረራ ነው፡፡
ደህንነቱ ባልተጠበቀ ሁኔታ ውስጥ ለወራት ተንገላተው የነበሩት ዜጎች መመለስ ትልቅ ነገር እንደሆነ የተናገሩት የድርጅቱ ዋና ዳይሬክተር አንቶኒዮ ቪቶሪኖ በቀጣዮቹ ወራት የሚመለሱ ዜጎች እንደሚኖሩ ተስፋ ማድረጋቸውን ገልጸዋል፡፡
ዋና ዳይሬክተሩ የሁለቱንም ሃገራት መንግስታት አመስግነዋል፡፡
ስደተኞቹ አስፈላጊውን የጤና ምርመራ ተደርጎላቸው ነው ወደ ኢትዮጵያ የተመለሱት፡፡ መንግስት በአዲስ አበባ ላቋቋመው እና ስደተኞቹ ተገልለው ለሚቆዩበት ለይቶ ማቆያ ማዕከል የገንዘብ ድጋፍ ማድረጉንም አይኦኤም አስታውቋል፡፡
አይኦኤም ከባለፈው ዓመት ጀምሮ ወደ ሃገራቸው የመመለስ ፍላጎት ያላቸውን 6 ሺ ገደማ ኢትዮጵያውያንን በባህር ዳርቻዋ ኤደን ከተማ መዝግቦ ነበር፡፡
ከነዚህ ውስጥ የ1 ሺ 100ውን ኢትዮጵያዊነት መንግስት አረጋግጧል፡፡ በቀጣዮቹ ጥቂት ሳምንታት ውስጥ መመለስ እንደሚጀምሩም ነው የተገለጸው፡፡
ተቋሙ ማሪብን በመሳሰሉ ሌሎች የየመን አካባቢዎች የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን ለመመለስ የሚያስችለውን ጥረት በቅርቡ እንደሚጀምር አስታውቋል፡፡
ድርጅቱ ባሳለፍነው ጥቅምት ይፋ እንዳደረገው መረጃ ከሆነ በኮሮና ወረርሽኝ የእንቅስቃሴ ገደቦች ምክንያት ለእንግልት የተዳረጉ 3 ሚሊዬን ገደማ ዜጎች ወደ ሃገራቸው ለመመለስ ይፈልጋሉ፡፡
ወደ የመን የሚሻገሩ ስደተኞች ቁጥር በእጅጉ ቀንሷል፡፡ እ.ኤ.አ በ2019 138 ሺ ገደማ የነበረው የስደተኞች ቁጥር በባለፈው የጎርጎሮሳውያኑ ዓመት ወደ 37 ሺ 500 አሽቆልቁሎ ነበር፡፡
ይህ ስደተኞቹ የመንን አቋርጠው ወደ ሳዑዲ አረቢያ ለመሻገር በመቸገራቸው፣ ለጉልበት ብዝበዛ እና ለተለያዩ ዓይነተ ብዙ ችግሮች በመዳረጋቸው ነው፡፡
ኑሮን ለማሸነፍ ሲሉ መዳረሻቸውን በውጭ ሃገራት የሚያደርጉ በርካታ ኢትዮጵያውያንም ሳዑዲ ለመግባት ሲሉ ባህር ተሻግረው በየመን ያቋርጣሉ፡፡ ይህ በርካቶችን ህይወት እስከማጣት ለደረሰ እንግልትና ስቃይ ዳርጓል፡፡
ወረርሽኙ ከተከሰተበት ጊዜ ጀምሮ 9 ሺ ገደማ ስደተኞች በህወጥ አዘዋዋሪዎች እጅ መውደቃቸውንም ነው የተቋሙ መረጃ የሚያመለክተው፡፡
በህገ ወጥ አዟዟሪዎች ወደ ባህር የሚወረወሩትን ጨምሮ ሰፊውን ውሃማ አካል ማቋረጥ በሚጠይቀው የጀልባ ጉዞ የባህር ሲሳይ ሆነው የቀሩ ጥቂት አይደሉም፡፡
ከጥቂት ሳምንታት በፊት በእንዲህ ዓይነት መንገድ 20 ስደተኞች ህይወታቸውን ማጣቸውን አይኦኤም ማስታወቁም የሚታወስ ነው፡፡