ድጋፎቹ የሚቆሙት በመንግስታቱ ድርጅት የገንዘብ እጦት ምክንያት ነው
ተመድ በየመን የሚያደርጋቸውን ሰብዓዊ ድጋፎች ሊያቆም ነው
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በገንዘብ እጦት ምክንያት በየመን የሚያደርጋቸውን የሰብዓዊ ድጋፎች ሊያቆም ስለመሆኑ ተሰምቷል፡፡
የድርጅቱ የሰብዓዊ ጉዳዮች ኃላፊ ማርክ ሎውኩክ በየመን ካሉት 41 የሰብዓዊ ድጋፍ ማዕከላት መካከል 31ዱ በመጪዎቹ ጥቂት ሳምንታት ውስጥ ሊዘጉ እንደሚችሉ አስጠንቅቀዋል፡፡
ሎውኩክ ይህ “የመን የኮሮና ወረርሽኝን ለመቋቋም እንድትችል በማሰብ የተጀመሩ ተግባራትን ለማቆም የሚያስገድድ ነው” ሲሉ ነው ለጸጥታው ምክር ቤት ያስታወቁት፡፡
ችግሩ የድርጅቱ የህጻናት ፈንድ በተለያዩ ግጭቶች እና ተፈጥሯዊ አደጋዎች ምክንያት ለተጎዱ ቤተሰቦች ያደርግ የነበረውን አስቸኳይ እርዳታ እንዲያቆም የሚያስገድድም ነው፡፡
ይህ ደግሞ አንድ ሚሊዬን ገደማ ተፈናቃዮች አስቸኳይ ድጋፍን ጨምሮ የኮሮና ወረርሽኝን ለመከላከል የሚያስችሉ መሰረታዊ የንጽህና መጠበቂያ ቁሳቁሶችን እንኳን እንዳያገኙ ሚያደርግ ነው እንደ ሎውኩክ ገለጻ፡፡
የተመጣጠነ የንጥረ ምግብ ይዞታ ያላቸውን ምግቦች ለማቅረብ የተጀመሩ የቤት ስራዎችም እክል ይገጥማቸዋል፡፡ በተመጣጠነ ምግብ እጥረት የሚሰቃዩ 260 ሺ ገደማ ህጻናትም የእክሉ ገፈት ቀማሽ ይሆናሉ፡፡ ይህ ደግሞ በተዘዋዋሪ መንገድ ኮሮናን እና ኮሌራን ለመሳሰሉ የተለያዩ የጤና እክሎች የመጋለጥ እድላቸውን ከፍ የሚያደርግ ነው፡፡
ታሞ መታከሙም ይቸግራል፤የሚያክሙ የጤና ተቋማትና ክሊኒኮችን ማግኘቱም ቀላል አይሆንም፡፡ ሎውኩክ በአስቸኳዩ የኮሮና ወረርሽኝ ምላሽ በኩል የሚሰጡ የጤና ግልጋሎቶች እስከ ወርሃ ሚያዚያ መጨረሻ እስከ 80 በመቶ ሊቀንሱ እንደሚችሉ ድርጅቱ ስለመገመቱም ተናግረዋል፡፡
እንደ ሲ.ጂ.ቲ.ኤን ዘገባ ከሆነ “ይህ ከአሁን ቀደም ያጋጠሙ በሽታዎችን በመከላከልና በመቆጣጠር ረገድ ትልቅ ሚና ሲጫወቱ የነበሩ የየአካባቢውን የጤና ቡድኖችን መበተን ነው፤ እነዚህን ቡድኖች ከምን ጊዜውም በላይ በአሁኑ ወቅት እንፈልጋቸዋለን፤ የምንፈልጋቸውም ኮሮና ለመቆጣጠር ብቻም ሳይሆን በዝናብ ወቅቶች እንደገና ሊቀሰቀስ የሚችለውን የኮሌራ ወረርሽኝ ለመከላከል ጭምር ነው” ሲሉ ሎውኩክ ያስቀምጣሉ፡፡
የድርጅቱ ተቋማትና ኤጀንሲዎች በበጀት እጥረት ውስጥ ሆነው ብዙ ርቀት ለመራመድ አይችሉም፡፡ የያዟቸውን የቤት ስራዎች ለመፈጸምም ይቸገራሉ፡፡
በየመን ብቻ እስከ ወርሃ ሃምሌ የሚዘልቅ ሰብዓዊ ድጋፍን ለማድረግ እስከ 900 ሚሊዬን ዶላር ያስፈልጋቸዋል፡፡
ሳዑዲ አረቢያ ባሳለፍነው ሳምንት ይህን ስጋት ሊያቀል የሚችል የ500 ሚሊዬን ዶላር ድጋፍን አድርጋለች፡፡ ኮሮናን ለመከላከል የሚውል የ25 ሚሊዬን ዶላር ድጋፍንም አድርጋለች፡፡ለዚህም ኃላፊው አመስግነዋል፡፡
“ድርጅቱ በሚጠበቀው ልክ እየተንቀሳቀሰ አይደለም፤የዓለም የጤና ድርጅትም ወደ ቻይና ያደላል” በሚል ተደጋጋሚ ትችቶች ሲቀርቡበት ሰንብተዋል፡፡
ይህንኑ ትችት ከሚሰነዝሩት አንዱ የሆኑት የአሜሪካው ፕሬዝዳንት ዶናልድ ትራምፕ ሃገራቸው ለዓለም የጤና ድርጅት የምታደርገውን የገንዘብ ድጋፍ ማቋረጧን ከሰሞኑ ማስታወቃቸውም የሚታወስ ነው፡፡