የዝንጆሮ ፈንጣጣን በሀገር ውስጥ መመርመር መጀመሩን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ
በ2014 ዓ.ም ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ዜጎች በወባ በሽታ መጠቃታቸው ሚኒስቴሩ ገልጿል
ባለፉት 30 ቀናት ውስጥ 40 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ተጠቅተው ህይወታቸው አልፏል ተብሏል
የዝንጆሮ ፈንጣጣ ናሙና በሀገር ውስጥ መመርመር መጀመሩን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር እና የሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በወቅታዊ የጤና ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥቷል፡፡
የጤና ጥበቃ ሚኒስትር ዴኤታ ዶክተር ደረጀ ድጉማ እንዳሉት የዝንጆሮ ፈንጣጣ ወረርሽኝ በመላው ዓለም በ59 ሀገራት ላይ ተከስቶ ሶስት ሞት ተመዝግቧል ብለዋል።
በኢትዮጵያ እስካሁን በላብራቶሪ የተረጋገጠ የዝንጆሮ ፈንጣጣ ታማሚ ያልተመዘገበ ሲሆን የበሽታው ቅኝት እና የመከላከል ስራው መቀጠሉንም ተናግረዋል፡፡
በሽታውን ለመከላከል ይቻል ዘንድም ከወጭ ሀገር ተመላሾች ለጥንቃቄ ሲባል የቆዳና ሌሎች የህመም ምልክቶች ሲገኝባቸው ከግለሰቦች ላይ ናሙና እየተወሰደ የምርመራና የክትትል ሥራዎች እየተሰሩ መሆኑንም ዶክተር ደረጀ ጠቁመዋል፡፡
በሽታውን በሀገር ውስጥ መለየት የሚያስችል የላብራቶሪ ምርመራ መደራጀቱን የገለጹት ዶክተር ደረጀ የተለያዩ የቅኝትና ምላሽ እንዲሁም የላብራቶሪ መመሪያዎች ተዘጋጅተዉ ለክልሎች ተሰራጭተዋል ብለዋል፡፡
የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ዶክተር መሳይ ሀይሉ በበኩላቸው ከሰኔ 17 እስከ ሐምሌ 18 ቀን 2014 ዓ.ም ባሉት ቀናት ውስጥ 40 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ምክንያት ሕይወታቸው ማለፉ ተረጋግጧል ብለዋል፡፡
ባለፉት 30 ቀናት ውስጥ በተደረገ የላቦራቶሪ ምርመራ 5 ሺ 300 ሰዎች የኮቪድ-19 ቫይረስ የተገኘባቸው ሲሆን 38 ሰዎች ደግሞ በጽኑ ህሙማን የሕክምና ክትትል ውስጥ ናቸውም ብለዋል፡፡
ከጥር 2014 ዓ.ም የኮቪድ-19 ማእበል በኋላ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች በከፍተኛ ደረጃ ቢቀንስም አሁን ላይ እየጨመረ በመሆኑ ህብረተሰቡ እንዲጠነቀቅ አሳስበዋል፡፡በሀገር አቀፍ ደረጃ የኮቪድ መከላከያ ክትባት የወሰዱ ሰዎች ቁጥር 43 ሚሊዮን ማለፉንም ኢንስቲትዩቱ አስታውቋል፡፡
የወባ በሽታ ተጠቂዎች እየጨመረ መሆኑን ያነሱት ዶክተር መሳይ በ2014 ዓ.ም ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን በላይ ሰዎች በዚሁ በሽታ ተጠቅተዋል ብለዋል፡፡
ለወባ በሽታ መጨመርም የበልግ ዝናብን ተከትሎ ከመጋቢት እስከ ግንቦት ባሉት ጊዜያት በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ፣ በደቡብ፣ ኦሮሚያ፣በአማራ እና በሲዳማ ክልሎች በመጨመሩ ነው፡፡