በአሜሪካ እና በአውሮፓ እየተስፋፋ ያለው የፈንጣጣ በሽታ ለኢትዮጵያ ስጋት መሆኑ ተገለጸ
በተደራጀ መንገድ ምላሽ ለመስጠት የቀድመ ዝግጅት ስራዎች እየተሰሩ እንደሆነም ነው የተገለጸው
በመግቢያ እና በመውጫ የኢትዮጵያ በሮች ላይ ክትትል እየተደረገ ነው ተብሏል
በአውሮፓ የበረታው ፈንጣጣ መሰል በሽታ (monkey pox) ለኢትዮጵያም ስጋት መሆኑን የህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ገለጸ፡፡
ከሰሞኑ አሜሪካን ጨምሮ በተለያዩ የአውሮፓ ሀገራት ፈንጣጣ መሰል የዝንጀሮ በሽታ በመስፋፋት ላይ ይገኛል፡፡
እስከዛሬ ድረስ በ12 ሀገራት ከ80 በላይ የዚሁ በሽታ ተጠቂዎች እንዳሉ የተገለጸ ሲሆን በሌሎች ሀገራት ላይም ተጨማሪ በሽተኞች ሊኖሩ እንደሚችሉ የዓለም ጤና ድርጅት ገልጾ ሁኔታውን እየተከታተለ እንደሚገኝ አስታውቋል፡፡
አል ዐይን አማርኛ የበሽታውን መስፋፋት ተከትሎ ለኢትዮጵያ ስጋት ይሆን ይሆን ሲል የኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩትን ጠይቋል፡፡
በኢንቲትዩቱ የቅድመ ማስጠንቀቂያ እና መረጃ ስርዓት አስተዳደር ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ዘውዱ አሰፋ ለአል ዐይን እንዳሉት ቫይረሱ ከዚህ በፊት ፈንጣጣ መሰሉ በሽታ ተጠቂ የሌለባቸው ሀገራት ሳይቀር እየተስፋፋ ነው፡፡
እንደማንኛውም ሀገር እኛም በቫይረሱ ስርጭት ስጋት አለን ያሉት አቶ ዘውዱ በኢትዮጵያ የመግቢያ እና መውጫ በሮች ላይ የተለመደው ክትትል እየተደረገ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በሀገሪቱ የየብስ እና የአየር ትራንስፖርት መግቢያ እና መውጫ ላይ ወደ ሀገር ውስጥ እንዳይገባ እና ወደ ሌሎች ሀገራት እንዳይሄድ የተላላፊ በሽታዎች ክትትል እየተደረገ መሆኑንም አቶ ዘውዱ ተናግረዋል፡፡
የበሽታው ተጠቂ በኢትዮጵያ ቢገኝ ማድረግ ስለሚገባን ስራዎች፣ ለህብረተሰቡ መሰጠት ስለሚገባው የግንዛቤ ፈጠራ መልዕክት እና የህክምና ክትትል ስራዎችን ለመለየት የቅድመ ዝግጅት ስራዎች በመሰራት ላይ እንደሆኑ አቶ ዘውዱ ጨምረው ገልጸዋል፡፡
ወረርሽኙ እስካሁን በእንግሊዝ፣ ስፔን፣ ፖርቹጋል ፣ ስዊዘርላንድ፣ ቤልጂየም፣ አሜሪካ፣ እስራኤል፣ ስኮትላንድ፣ አውስትራሊያ እና በሌሎችም ሃገሮች ሪፖርት ተደርጓል፡፡
ከ80 በላይ ሰዎችን ያጠቃም ሲሆን ከዚህ በፊት በሽታው ለመጀመሪያ ጊዜ የታየው በማዕከላዊ እና ምዕራብ አፍሪካ በዝንጆሮዎች ላይ ነበርም ተብሏል፡፡ በሽታው በአካላዊ ንኪኪ ከሰው ወደ ሰው የሚተላለፍ ሲሆን በቫይረሱ የተያዘ ሰው 10 በመቶ የመሞት እድል እንዳለው ተገልጿል፡፡
ወረርሽኙ ከዚህ በፊት ስምንት ጊዜ በዓለማችን ላይ የተከሰተ ሲሆን አሁን ደግሞ በፖርቹጋል አምስት ሰዎች፣ በስፔን 23 ሰዎች የበሽታውን ምልክት ማሳየታቸውን ተከትሎ እንዲለዩ መደረጉ ተገልጿል፡፡በእንግሊዝ ዘጠኝ ሰዎች ተጠቅተዋልም፡፡
በአሜሪካ ደግሞ አንድ ሰው በዚህ ተላላፊ በሽታ የተጠቃ ሰው የተገኘ ሲሆን ከቫይረሱ ተላላፊነት አንጻር ተጨማሪ በሽተኞች ሊኖሩ እንደሚችሉ ተገምቷል፡፡ በሽታው ለመጀመሪያ ጊዜ እንደ ጎርጎሮሳውያኑ ዘመን አቆጣጠር በ1958 በዝንጀሮ ላይ ነበር የተገኘው፡፡
ሆኖም አሁን ላይ የበሽታው መከሰት መታወቁን ተከትሎ ሰዎቹ እንዴት ሊጠቁ እንደቻሉ ተመራማሪዎች እርግጠኛ መሆን አልቻሉም፡፡
ተመራማሪዎቹ እስካሁን በዚህ ቫይረስ መጠቃታቸውን ያላወቁ ሰዎች ሊኖሩ ይችላሉ የሚል ጥርጣሬ ያላቸው ሲሆን ሰዎች የተለየ ስሜት ከተሰማቸው ወደ ጤና ተቋም እንዲመጡ አሳስበዋል፡፡