ኢትዮጵያ ሁለተኛውን የሩሲያ-አፍሪካ ጉባኤ በአዲስ አበባ ለማካሄድ ዝግጁ መሆኗን አስታወቀች
አቶ ደመቀ መኮንን ሞስኮን እንዲጎበኙ በሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ግብዣ ቀርቦላቸዋል
ም/ጠ/ሚ እና የውጭ ጉ/ሚ ደመቀ መኮንን ከሩሲያ-አፍሪካ የትብብር ጉባኤ ዋና ጸሐፊ ሚስተር ኦሌግ ጋር ተወያይተዋል
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ከሩሲያ-አፍሪካ የትብብር ጉባኤ ዋና ጸሐፊ ሚስተር ኦሌግ ኦዝሮቭ ጋር ተወያይተዋል።
መሪዎቹ የተወያዩት በቀጣይ ዓመት በአፍሪካ ሊካሄድ ስለታሰበው ሁለተኛው የሩሲያ-አፍሪካ ጉባኤ ዙሪያ ሲሆን ኢትዮጵያ ጉባኤውን ለማዘጋጀት ዝግጁ መሆኗን ገልጻለች።
ሚስተር ኦሌግ ስለ ሩሲያ-አፍሪካ የትብብር ጉባኤ ስራዎች እና ሁለቱ ወገኖች ስለሚተባበሩባቸው አጀንዳዎች ዙሪያ እንዲሁም ስለጉባኤው አላማዎች ለአቶ ደመቀ ገለጻ ማድረጋቸውን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ ጽህፈት ቤት አስታውቋል።
መሪዎቹ ሁለቱ አገራት በቴክኖሎጂ ፣ በጸጥታ እና ደህንነት ፣ በግብርና ፣ በኑክሌር ቴክኖሎጂ እና ህክምና ዘርፎች ላይ በጋራ መስራት በሚችሉባቸው አጀንዳዎች ዙሪያ መወያየታቸው ተገልጿል።
የሩሲያ-አፍሪካ የትብብር ጉባኤ ዋና ጸሀፊ የሆኑት ሚስተር ኦሌግ ኦዝሮቭ አቶ ደመቀ መኮንን ሞስኮን እንዲጎበኙ በሩሲያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ግብዣ እንደቀረበላቸው ተናግረዋል።
ኢትዮጵያ ከሩሲያ ጋር ያላትን ግንኙነት ማሳደግ እንደምትፈልግም የተናገሩት አቶ ደመቀ ፣ ሩሲያ ጉባኤው በአፍሪካ እንዲካሄድ መወሰኗን ስለማድነቃቸው የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በድረገጹ አስታውቋል።
የመጀመሪያው የአፍሪካ-ሩሲያ ጉባኤ ባሳለፍነው ዓመት በሩሲያ ሱቺ ከተማ የተካሄደ ሲሆን በዚህ ጉባኤ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ መገኘታቸው እና ከሩሲያ ፕሬዘዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በሁለትዮሽ እና ዓለም አቀፍ ጉዳዮች ዙሪያ መወያየታቸው አይዘነጋም።