ኢትዮጵያ ልታለማ ያቀደችውን የኒውክሌር ኃይል የተመለከቱ ሁለት ስምምነቶችን ከሩሲያ ጋር አደረገች
ኒውክሌርን ለልማት ለመጠቀም ያስችላል የተባለለት የትብብር ስምምነት ረቂቅ አዋጅ በፓርላማ መጽደቁ የሚታወስ ነው
ስምምነቶቹ የኑክሌር ኃይልን በተመለከተ አዎንታዊ የህዝብ አመለካከትን ለመገንባት የሚያስችሉ ናቸው ተብሏል
ኢትዮጵያ ልታለማ ካቀደችው የኒውክሌር ኃይል ጋር በተያያዘ ከሩሲያ ጋር ሁለት የመግባቢያ ስምምነቶችን አደረገች፡፡
ስምምነቶቹ ለሰላማዊ ግልጋሎት እንዲለማ የተፈለገውን የኑክሌር ኃይል አስመልክቶ አዎንታዊ የህዝብ አመለካከትን ለመገንባት የሚያስችሉ ነው፡፡
በአቅም ግንባታም ላይ ያተኩራሉ።
በኢትዮጵያ የኑክሌር ኃይል መስክ በትምህርትና ስልጠና ዙሪያ ትብብር ለማድረግ ያግዛሉም ተብሏል፡፡
የመግባቢያ ስምምነቶቹን በሩሲያ የኢትዮጵያ አምባሳደር አለማየሁ ተገኑ እና የሩሲያ አቶሚክ ኢነርጂ ተቋም (ሮሳቶም) ምክትል ዋና ዳይሬክተር ኒኮላ ስፓስኪ ትናንት ተፈራርመዋል፡፡
ኢትዮጵያ 95 በመቶ ያህል የኃይል ፍላጎቷን ከኤሌክትሪክ አማራጭ ነው የምታገኘው፡፡ ታዳሽ የኃይል አማራጮችንም ትጠቀማለች፡፡
ሆኖም ከየአማራጩ የሚገኘው የኃይል አቅርቦት ከፍላጎቱ በተለይም እያደገ እንደሚሄድ ከሚነገርለት የአምራች ተቋማት የኃይል ፍላጎት ጋር ሊጣጣም አልቻለም፡፡
የማይቋረጥ የኃይል አማራጭን መጠቀምም አስፈልጓል፡፡ ለዚህ ምላሽ ሊሰጥ የሚችል አማራጭ ሆኖ የተገኘው የኒውክሌር ኃይል አማራጭ ነው፡፡
ኢትዮጵያ ኒውክሌርን በኃይል አማራጭነት ለመሻት መፈለጓን ከመግለጽ በዘለለ ተግባራዊ እንቅስቃሴዎችን ማድረግ መጀመሯን ደጋግማ አስታውቃለች፡፡
እንደመጀመሪያ ምዕራፍ የሚቆጠረውን የኢትዮጵያ የኒውክሌር ሳይንስ እና ቴክኖሎጂ ተቋም በማቋቋም ላይ እንደምትገኝም በሃገር አቀፍ ደረጃ የተቋቋመው ግብረኃይል አስታውቆ ነበር፡፡
የኒውክሌር ኃይልን ለልማት ለመጠቀም የሚያስችለው የትብብር ስምምነት ረቂቅ አዋጅ ታህሳስ 2013 ዓ/ም ላይ በፓርላማ መጽደቁ የሚታወስ ነው፡፡
ይህን ተከትሎም ኢትዮጵያ የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ተቋማትን ለመገንባት የሚያስችሉ ስምምነቶችን ከሩሲያ ጋር ስታደርግ ቆይታለች፡፡
ይህ የአሁኑ የመግባቢያ ስምምነትም በዘርፉ እንደሚደረጉ ከተነገረላቸው ተጨማሪ አዳዲስ ስምምነቶች መካከል ነው፡፡
ከሰሞኑ ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ቆይታ ያደረጉት በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኤቭጄኒ ቴሬኪን “ኢትዮጵያ የኒውክሌር ተጠቃሚ ሃገሮች አባል ከሆነች እኛ ለመርዳት ዝግጁ ነን” ሲሉ ተናግረዋል፡፡
የኒውክሌር ኃይል ማመንጫ ተቋማትን ለመገንባት እስከ አስር የሚደርሱ ዓመታት ሊያስፈልጉ ይችላል፡፡
ሆኖም እስከዚያው ቴክኖሎጂውን ለተለያዩ ግልጋሎቶች ለመጠቀም ይቻላል፡፡
የኢትዮጵያ ጨረራ መከላከል ባለስልጣን ኢትዮጵያ ኒውክሌርን ለካንስር ህክምና፣ ለቆላ ዝንብ ማምከኛ እና ለመንገድ ስራ በአግባቡ እየተጠቀመችበት እንደምትገኝ ከአሁን ቀደም ማስታወቁ የሚታወስ ነው፡፡