ኢትዮጵያ የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ቢሮ ስብሰባ እንዲጠራ መጠየቅ ድርድሩን ለማስቀጠል መፍትሄ እንደሚሆን አስታወቀች
የሶስትዮሽ የግድቡ ውይይት ከሁለት ሳምንት በፊት በኪንሻሳ ተካሂዶ ነበር
ኢትዮጵያና ግብጽ ”በዝግ ይምከሩ” የሚለውን የሱዳን ሀሳብ ኢትዮጵያ አልተቀበለችም
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ባወጣው መግለጫ የግድቡን የሶስትዮሽ ድርድር ለማስቀጠል፤ የአፍሪካ ህብረት ጉባኤ ቢሮ ስብሰባ እንዲጠራ ማድረግ መፍትሄ እንደሚሆን ኢትዮጵያ አስታውቃለች፡፡
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የሶሰትዮሽ ድርድር ከሁለት ሳምንት በፊት በወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር እና የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ፕሬዘዳንት ፌሊፕ ቴሽኬዲ ሰብሳቢነት በኬንሻሳ መካሄዱ ይታወሳል።
በድርድሩ ሂደት ግብጽ እና ሱዳን የታዛቢዎች ሚና ከፍ ማለት አለበት የሚል ጥያቄ ሲያንጸባርቁ ኢትዮጵያ ደግሞ ድርድር ከአፍሪካ ህብረት ውጪ መካሄድ የለበትም የሚል ጹኑ አቋም ይዛለች፡፡
ኢትዮጵያ የታዛቢዎች ሚናም አሁን ባለው ሁኔታ መቀጠል አለበት የሚል አቋም በማራመዷ ምክንያት ድርድሩ ያለስምምነት እንደተጠናቀቀ በወቅቱ መገለጹ ይታወሳል።
የሱዳኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብደላ ሀምዶክ ባሳለፍነው ሳምንት የኢትዮጵያ ግብጽ እና ሱዳን መሪዎች በግድቡ ዙሪያ በዝግ እንዲመክሩ ጥሪ ማቅረባቸው ይታወሳል።
ኢትዮጵያ በሱዳን የቀረበላትን በዝግ እንወያይ ጥያቄ እንዳልተቀበለች ያስታወቀች ሲሆን አሁንም የግድቡ ድርድር በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት እንዲቀጥል እና የአሜሪካ አውሮፓ ህብረት እና ደቡብ አፍሪካ በታዛቢነት እንዲቀጥሉ እንደምትፈልግ ለሱዳን ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብደላ ሐምዶክ በጻፈቸው ደብዳቤ ማሳወቋን የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።