ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ፍሰት ማነቆ የሆኑ 80 ህጎች ማሻሻሏን አስታወቀች
የሰላም ስምምነት መፈረሙን ተከትሎ በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ፍሰት መጨመሩ ተገለጸ

የሰላም ስምምነት መፈረሙን ተከትሎ በኢትዮጵያ የኢንቨስትመንት ፍሰት መጨመሩ ተገለጸ
ኢትዮጵያ ለኢንቨስትመንት ፍሰት ማነቆ የሆኑ 80 ህጎች ማሻሻሏን አስታወቀች፡፡
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን እንዳለው ለንግድ እና ኢንቨስትመንት አመቺ ያልሆኑ ህጎች መሻሻላቸውን አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን በኢትዮጵያ ኢንቨስት አድርጉ የተሰኘ ዓለም አቀፍ አውደ ርዕይ ማዘጋጀቱን ገልጿል፡፡
ምክትል ኮሚሽነር አቶ ተመስገን ጥላሁን ጉዳዩን አስመልክተው በሰጡት መግለጫ ከሚያዝያ 18-20 ቀን 2015 ዓ.ም በአዲስ አበባ የኢትዮጵያን ኢንቨስትመንት ማስፋፋት ዓላማ ያደረገ አውደር ዕይ ላይ ተዘጋጅቷል።
በዚህ አውደ ርዕይ ላይ ከ600 በላይ ዓለም አቀፍ ኩባንያዎች እና የቢዝነስ ሰዎች እንደሚሳተፉ ይጠበቃል ያሉት አቶ ተመስገን በመላው ዓለም ያሉ የኢትዮጵያ ኢምባሲዎች እና ዲፕሎማቶች ተጨማሪ ተሳታፊዎችን እያሳመኑ እና እየመለመሉ ነውም ብለዋል፡፡
እስካሁን ባለው ጥረትም ከ500 በላይ ተሳታፊዎች በኢንቨስትመንት አውደ ርዕዩ ላይ እንደሚሳተፉ ማረጋገጫ መስጠታቸውንም አክለዋል፡፡
በየዓመቱ በኢትዮጵያ በቋሚነት እንዲካሄድ የታሰበው ይህ የኢንቨስትመንት አውደ ርዕይ ዘንድሮ ብቻ ከ3 ቢሊዮን በላይ ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ታቅዷል ተብሏል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ ግን በኢትዮጵያ ባሉ የኢንቨስትመንት ስራዎች ላይ እንቅፋት ይፈጥሩ የነበሩ ህጎች መሻሻላቸውን አቶ ተመስገን ተናግረዋል፡፡
ለአብነትም በኢትዮጰያ ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ ባለሃብቶች የተከለከሉ እና የተፈቀዱ የኢንቨስትመንት ስራዎችን በግልጽ በኢንቨስትመንት ፖሊሲው ላይ እንዲቀመጡ መደረጉ በመግለጫው ላይ ተጠቅሷል፡፡
በአጠቃላይ ኢትዮጵያ ባለፉት ሁለት ዓመታት ውስጥ 80 ህጎችን ለኢንቨስትመንት አመቺ በሚሆኑበት መንገድ እንዲሻሻሉ መደረጋቸውን ምክትል ኮሚሽነሩ ጠቁመዋል፡፡
አቶ ተመስገን አክለውም በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረው ጦርነት የሀገር ውስጥ እና የውጭ ባለሀብቶችን ተጨማሪ ሀብት እንዳያፈሱ እና ፍላጎት እንዲያጡ ማድረጉን ተናግረዋል፡፡
ጦርነቱን ማቆም የሚያስችል የሰላም ስምምነት መፈረሙን ተከትሎ ከዚህ በፊት በሂደት ላይ የነበሩ እና ተጨማሪ አዳዲስ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ኩባንያዎች በሀገሪቱ የተለያዩ አካባቢዎች በመሰማራት ላይ መሆናቸውንም አቶ ተመስገን ገልጸዋል፡፡
ኢትዮጵያ በተያዘው የ2015 በጀት ዓመት 6 ነጥብ 1 ቢሊዮን ዶላር የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት ለመሳብ ያቀደች ሲሆን እስከ ጥር ወር ድረስ ብቻ 2 ነጥብ 3 ቢሊዮን ዶላር መሳቧ ተገልጿል፡፡