የሩስያ ጋዝ ላይ የሚጣሉ እገዳዎች መካከለኛው አውሮፓ ኢኮኖሚን ክፉኛ እንደሚጎዳ ተገለፀ
ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም በሰራው ጥናት የጋዝ እገዳው የሀገራቱን አመታዊ የምርት እድገት ይጎዳል
ጣሊያና፣ ሃንጋሪ፣ ስሎቫኪያ፣ ቼክ ሪፐብሊክና ጀርመን በሩሲያ ጋዝ እገዳ ከፍተኛ ጉዳት ሊያስተናግዱ ይችላሉ
ዓለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (አይ.ኤም.ኤፍ) በሩሲያ ጋዝ ላይ የሚጣሉ እገዳዎች መካከለኛው አውሮፓን ክፉኛ ይጎዳል ሲል አሳሰበ።
ተቋሙ ባወጣው ጥናተ ውጤት የሩስያ የተፈጥሮ ጋዝ እገዳ በሃንጋሪ፣ ስሎቫኪያ፣ ቼክ ሪፐብሊክ እና ጣሊያን ውስጥ ከፍተኛ የኢኮኖሚ ውድቀት እንደሚያመጣ አስጠንቅቋል።
- ጀርመን፤ የሩሲያ ጋዝ ወደ ሀገሯ በበቂ ሁኔታ ካልገባ ኢንዱስትሪዎች ሊዘጉ ይችላሉ ስትል አስጠነቀቀች
- ሩሲያ ወደ ጀርመን የሚያልፉ የጋዝ ማስተላለፊያዎቿን መዝጋት ጀመረች
የሩሲያ የተፈጥሮ ጋዝ ሲቋረጥ አንዳንድ ሀገራት ከመደበኛ የጋዝ ፍጆታ እስከ 40 በመቶ የሚደርስ እጥረት ሊገጥማቸው እንደሚችልም ገልጸዋል።
የሩሲያ የተፈጥሮጋዝ ከተቋረጠ በአንዳንድ ሀገራት ላይ አጠቃላይ የሀገር ውስጥ የምርት እድግት እስከ 6 በመቶ ሊቀንስ እንደሚችልም አይ.ኤም.ኤም አመላክቷል።
ፈሳሽ የተፈጥሮ ጋዝን (LNG) ጨምሮ የጋዝ አቅርቦቶች ወደሚፈለጉበት ቦታ በነፃነት እንዳይፈስ ከተከለከሉ ስሎቫኪያ፣ ቼክ ሪፐብሊክ እና ጣሊያን የሀገር ውስጥ ምርት በ5 በመቶ ሊቀንስ እንሚችልም በጥናቱ ተገልጿል።
የሩሲያ የተፈጥሮ ጋዝ ከተቋረጠ የጀርመን የሀገር ውስጥ ምርት በከፍተኛው እና አስከፊ በሆነ ሁኔታ እስከ 2 በመቶ ድረስ ሊቀንስ ይችላልም ተብሏል።
እንዲሁም በፈረንጆቹ በ2023 የጀርመን ኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በ2.7 በመቶ ሊቀንስ እንደሚችልም በጥናቱ ተመላክቷል።
ጀርመን ከዚህ ቀደም የሩሲያ ጋዝ ወደ ሀገሯ በበቂ ሁኔታ ካልገባ ኢንዱስትሪዎች ሊዘጉ ይችላሉ ስትል ማስጠንቀቋ ይታወሳል።
የሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነትን ተከትሎ በሩሲያ ላይ ከ6 ሺህ በላይ ማዕቀቦች የተጣሉ ሲሆን ከ300 በላይ ዲፕሎማቶቿ ደግሞ ከተለያዩ ሀገራት ተባረው ወደ ሞስኮ ተመልሰዋል።
ሩሲያም የአጻፋ እርምጃ በመውሰድ ነዳጅ ገዢ ሀገራት በሩብል እንዲገዙ ውሳኔንም ያሳለፈች ሲሆን ጀርመን እና ጣልያን ማዕቀቡን ሳይጥሱ ከሩሲያ ነዳጅን በሩብል ለመግዛት ወስነው ነበር።
40 በመቶ የአውሮፓ ሀገራትን የነዳጅ ፍላጎት የምታሟላው ሩሲያ ናት።