“ኢትዮጵያ በሕዳሴ ግድብ እና ከፊታችን ባለው ምርጫ ምክንያት ፈተና በዝቶባታል”-ጠ/ሚ ዐቢይ አሕመድ
ለ1442ኛው የዒድ አል ፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተላልፈዋል
ጠ/ሚኒሰትሩ “አሁን ያለው የኢትዮጵያ ሁኔታ ለግል ሳይሆን ለጋራ ህልውናችን እንድናስብ የሚያስገድደን ነው” ብለዋል
ጠ/ሚኒሰትሩ “አሁን ያለው የኢትዮጵያ ሁኔታ ለግል ሳይሆን ለጋራ ህልውናችን እንድናስብ የሚያስገድደን ነው” ብለዋል፡፡ ለ1442ኛው የዒድ አል ፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክትም ጠቅላይ ሚኒስትሩ አስተላልፈዋል፡፡
ኢትዮጵያ አሁን ላይ በሕዳሴ ግድብ እና ከፊታችን ባለው ምርጫ ምክንያት ፈተና ላይ መሆኗን ጠቅላይ ሚኒሰትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ገለፁ፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ 1442ኛውን የዒድ አል ፈጥር በዓል ምክንያት በማድረግ ባስተላለፉት መልእክት እንደገለፁት ፤ አሁን ያለው የኢትዮጵያ ሁኔታ ለግል ሳይሆን ለጋራ ህልውናችን እንድናስብ የሚያስገድደን፣ ከግል ምቾታችን በላይ ለጋራ ደኅንነታችን እንድንተጋ በእጅጉ ግድ የሚልበት ጊዜ ነው ብለዋል፡፡
“መዋኛችን ድፍርስ፣ መንገዳችን እሾህ የበዛበት መሆኑን እናውቃለን። በመንገዳችን ላይ እንቅፋቶችን የሚያኖሩ፣ ወደኋላ የሚጎትቱን፣ ተስፋችንን ሳናይ በፊት ተሰብረን እንድንወድቅ መሠረታችንን የሚገዘግዙ ኃይሎች፣ ከውጭም ከሀገር ውስጥም በርትተው የመጡበት ፈታኝ ጊዜ ነው”ም ነው ያሉት ጠቅላይ ሚኒሰትሩ፡፡
አሁን ላይ ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድብ እና ምርጫ ምክንያት ፈተና እንደበዛባትም ዶ/ር ዐቢይ ጠቅሰዋል፡፡
ኢትዮጵየሕዳሴ ግድቡን እና ምርጫውን ማሳካት ከቻለች ለኢትዮጵያውያን ቀላል የማይባሉ የስኬት በሮች እንደሚከፈቱ እናውቃለን ያሉት ዶ/ር ዐቢይ ፤ ምርጫውን በስኬት ማከናወን በኢትዮጵያ አዲስ የዴሞክራሲ ምዕራፍ እንደሚከፍት እንዲሁም የሕዳሴ ግድብ መጠናቀቅም ግዙፍ የብልጽግና ፋና እንደሚለኩስ ገልፀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒሰትሩ “ሁለቱ ግዙፍ ፕሮጀክቶች ያላቸው አስተዋጽኦ ከማይዋጥላቸው ኃይሎች” ኢትዮጵያ ተከታታይ ትንኮሳዎች እየተቃጡባት መሆኑንም ነው የገለፁት፡፡
እነዚህን ትንኮሳዎች በመመከት በኩል ጥቂት የማይባሉ አርቆ አስተዋይ ዜጎቻችን በሀገር ውስጥና በውጭ መድረኮች ትልልቅ ጀብዶችን እየፈጸሙ ይገኛሉም ብለዋል ዶ/ር ዐቢይ፡፡
ሁሉም ኢትዮጵያውያን መሰል ርብርብ ቢያደርጉ ለዘመናት የሀገሪቱ ችግሮች ፈውስ የሚሆን አቅም መፍጠር እንደሚቻል ያላቸ,ቸውን እምነትም ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ገልፀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለ1442ኛው ዒድ አል ፈጥር በዓል የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክትም አስተላልፈዋል፡፡