የትግራይ ታጣቂዎች በሱዳን ጦርነት መሳተፍ አለመሳተፋቸው እየተጣራ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር አስታወቀ
ኢትዮጵያ ምዕራባዊያን ሀገራት "በደቦ" መግለጫ ከማውጣት እንዲቆጠቡ ጠይቃለች
በአውሮፓ ሀገራት የመኖሪያ ፈቃድ ካላገኙ ዜጎች መካከል 15ቱን ወደ ኢትዮጵያ መመለሳቸው ተገልጿል
የትግራይ ታጣቂዎች በሱዳን ጦርነት መሳተፍ አለመሳተፋቸው እየተጣራ መሆኑን የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር አስታወቀ።
የውጭ ጉዳይ ሚንስቴር ቃል አቀባይ አቶ ነብዩ ተድላ በወቅታዊ የዲፕሎማሲ ጉዳዮች ዙሪያ መግለጫ ሰጥተዋል።
በመግለጫው ላይ ኩተነሱ ጉዳዮች መካከልም የትግራይ ታጣቂዎች በሱዳን ጦርነት ተሳትፈዋል ፣ የአውሮፓ ህብረት በኢትዮጵያ ላይ ስለጣላቸው ገደቦች፣ በኢትዮጵያ ላይ ስለሚወጡ የደቦ መግለጫዎች፣ የሱዳን ጦርነት እና ሌሎችም ተጠቃሽ ናቸው።
የሚንስቴሩ ቃል አቀባይ አቶ ነብዩ ተድላ እንዳሉት ከሰሞኑ የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳድር ስላስተባበለው የትግራይ ታጣቂዎች ከሱዳን ብሔራዊ ጦር ጋር ተሰልፈው የፈጥኖ ደራሽ ሀይሎችን እየወጉ ነው በሚለው ጉዳይ ላይ ከጋዜጠኞች ለቀረበላቸው ጥያቄ ምላሽ ሰጥተዋል።
ቃል አቀባዩ በምላሻቸው ጉዳዩን እንደሰሙ ነገር ግን እንደ ሀገር ኢትዮጵያዊያን ታጣቂዎች በሱዳን ጦርነት ውስጥ መሳተፍ አለመሳተፋቸው እየተጣራ መሆኑን ተናግረዋል።
"ታጣቂዎቹ በሱዳን ጦርነት መሳሰተፍ አለመሳተፋቸው ከተጣራ በኋላ መረጃውን ይፋ እናደርጋለን" ሲሉም አቶ ነብዩ በምላሻቸው ላይ ጠቅሰዋል።
ሌላኛው ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው ካነሷቸው ጉዳዮች መካከል የዓለም ፕረስ ነጻነት ቀንን በማስመልከት ምዕራባዊያን ሀገራት በኢትዮጵያ ላይ ያወጡት መግለጫ ነው።
"ኢትዮጵያ መግለጫውን ካወጡት እያንዳንዳቸው ሀገራት ጋር የሁለትዮሽ ስምምነት አላት፣ ግንኙነታችን የሚመራው በዚህ ሆኖ ሳለ በኢትዮጵያ ጉዳይ መግለጫ በደቦ ማውጣት እንደ ማስፈራራት ይቆጠራል" ብለዋል አቶ ነብዩ።
የአውሮፓ ህብረት መኖሪያ ፈቃድ ሳይኖራቸው በአውሮፓ ሀገራት የሚኖሩ ኢትዮጵያዊያንን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ኢትዮጵያ ተባባሪ አይደለችም በሚል ያሳለፈው ውሳኔ ተገቢነት የጎደለው እንደሆነም ተገልጿል።
ቃል አቀባዩ በመግለጫቸው ላይ እንዳሉት "የአውሮፓ ህብረት 86 ሰዎች ኢትዮጵያዊያን ናቸው ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ አድርጉ ሲሉን መጀመሪያ እነዚህ ዜጎች ዜግነታቸው ኢትዮጵያዊ መሆናቸውን ማረጋገጥ አለብን በሚል ባደረግነው ማጣራታም 26ቱ ብቻ ኢትዮጵያዊ ሆነው ተገኝተዋል" ብለዋል።
በአውሮፓ ሀገራት ይኖሩ የነበሩ እና የመኖሪያ ፈቃድ ካላገኙ መካከል 15 ኢትዮጵያዊያን ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ መደረጉንም አቶ ነብዩ ተናግረዋል።
ይህን ሁሉ ጥረት እያደረግን ህብረቱ ኢትዮጵያ ተባባሪ አልሆነችም በሚል በኢትዮጵያውያን ቪዛ አመልካቾች ላይ የቪዛ ገደብ መጣሉ አግባብ ነው ብለን እናምንም ሲሉም ቃል አቀባዩ አክለዋል።
በአውሮፓ ህብረት አዲስ የቪዛ ገደብ ውሳኔ መሰረት የቪዛ ማመልከቻ ጊዜን ከ15 ቀናት ወደ 45 ቀናት ከፍ ያደረገ ሲሆን ቪዛው ለአንድ ጊዜ መግቢያ ብቻ እንዲሆንም ወስኗል።