የዩኒቨርስቲ መውጫ ፈተና ያላለፉ ተማሪዎች እጣፋንታ ምን ይሆናል?
ትምህርት ሚንስቴር “በአቋራጭ ድግሪ ማግኘት” ያበቃል ብሏል
የዩኒቨርስቲ መውጫ ፈተና ውጤት የትምህርት ስብራትን የሚያሳይ መሆኑን ሚኒስቴሩ ገልጿል
በ2015 ዓ.ም ለመጀመሪያ ጊዜ የተሰጠው የዩኒቨርስቲ የመውጫ ፈተና የሀገሪቱ የትምህርት ደረጃ ያለበትን ሁኔታ ፍንትው አድርጎ ማሳየቱን ትምህርት ሚንስቴር ተናግሯል።
ፈተናውን ከወሰዱ 150 ሽህ ገደማ ተማሪዎች ውስጥ 40 በመቶዎቹ ብቻ ማለፋቸውን ሚንስቴሩ አስታውቋል።
ከሰኔ 30 እስከ ሀምሌ 7፤ 2015 ዓ.ም ድረስ የተሰጠው ፈተና ውጤት ትምህርት ሚንስቴር ‘ከጠበቀው በላይ’ እንዳገኘው ለአል ዐይን አማርኛ ገልጿል።
ውጤቱን ተንትኖ ሙሉ ምስሉን ገና እንዳልተረዳ የተናገረው ሚንስቴሩ፤ ሆኖም ውጤቱ እንደ “ስጋቴ” አይደለም ሲል፤ ከተገኘው በታች ጠብቆ እንደነበር ጠቁሟል።
የአካዳሚ ጉዳዮች መሪ ስራ አስፈጻሚ የሆኑት ዶ/ር ኤባ ሚጃና የመውጫ ፈተናው የመጀመሪያ ጊዜ እንደመሆኑ ከፍ ያለ ውጤት ላይመጣ ይችላል የሚል ስጋት ነበር ብለዋል።
ሆኖም አጠቃላይ ውጤቱ የሀገሪቱን የትምህርት ስብራት የሚያሳይ መሆኑን ስራ አስፈጻሚው ለአል ዐይን ተናግረዋል።
“ትምህርቱ ምን ደረጃ ላይ እንዳለ የሚያሳይ በጣም ግልጽ የሆነ አመላካች ነው። አሁን ያለው አስተሳሰብ (ሁሉንም ማለት ባያስችልም) በስርቆት ላይ የተመሰረተ፣ በየደረጃው ራሱን ችሎ፣ አንብቦ፣ አውቆ ወደ ሚቀጥለው ደረጃ ማለፍ ሳይሆን አንዱ ከሌላው ኮርጆ ወይም ፈተና ሰርቆ ለማለፍ የሚሞከርበት ላይ ነው የደረስነው” በማለት ገልጸል።
ትምህርት ሚንስቴር በ2015፤ 240 ሽህ የሚሆኑ ተማሪዎች የመውጫ ፈተና ይወስዳሉ ብሎ ጠብቆ፤ ለመፈተን ብቁ የሆኑት ግን 194 ሽህ መሆናቸውን አስታውቋል። ከእነዚህም ውስጥ ደግሞ ለፈተና የተቀመጡት 150 ሽህ184 መሆናቸውን ታውቋል። 50 እና ከዚያ በላይ ሆኖ በተቆረጠው የማለፊያ ነጥብ 61 ሽህ ገደማ ተማሪዎች ብቻ (40.6 በመቶ) አልፈዋል።
የግል ተቋማት ካስፈተኗቸው 62 ሽህ ገደማ ተማሪዎች ማለለፍ የቻሉት 12 ሽህዎቹ ብቻ መሆኑን ትምህርት ሚንስቴር ገልጿል።
ያላለፉ ተማሪዎች እጣ ፋንታስ ምንድን ነው ሲል አል ዐይን ላነሳላቸው ጥያቄ ዶ/ር ኤባ ሚጃና፤ እስኪያልፉ ድረስ “ያለገደብ” መፈተን ይችላሉ ብለዋል።
“በዓመት ሁለት ጊዜ ነው የምንሰጠው። በመጀመሪያው ያልተሳካለት በሁለተኛው መፈተን ይችላል። ከዚያ በሚቀጥለው ዓመትም ስዘጋጅ እፈተናለሁ ካለ መብቱ ነው። ስለዚህ ገደብ የለውም” ብለዋል።
ከዚህ ቀደም የመውጫ ፈተና የሚወስዱ የህግና የጤና ተማሪዎች ሁለት ፈተና እንዳልወሰዱ የጠቀሱት ስራ አስፈጻሚው፤ የፈቃድ ፈተና ግን ከሚመለከታቸው ተቋማት እንደሚወስዱ ገልጸዋል።
ኃላፊው ተማሪዎቻቸውን የማያበቁ የመንግስትም የግልም የትምህርት ተቋማት ከዚህ በኋላ አይቀጥሉም ብለዋል። ውጤቱ እውቅና ከመስጠት ጀምሮ ተማሪዎችን እስከመመደብ ድረስ እንደሚታይ ገልጸው፤ በሚቀጥሉት ዓመታት ጥብቅ አሰራርን በመዘርጋት የተሻለ ፈተና እንደሚሰጥም ተናግረዋል።
የመውጫ ፈተናን ለማዘጋጀት ለቅድመ ዝግጅት ሰፋ ያለ ጊዜ መሰጠቱን ትምህርት ሚንስቴር ተናግሯል። 215 ፈተናዎች ተዘጋጅቶ፣ ተገምግሞና አስተችቶ መቅረቡን የጠቀሱት የሚንስቴሩ የአካዳሚ ጉዳዮች መሪ ስራ አስፈጻሚ ዶ/ር ኤባ ሚጃና ፤ ቅሬታ በአንድ ፈተና ላይ ብቻ መምጣቱን ተናግረዋል። ዩኒቨርስቲዎች በአንዳንድ ፈተናዎች ላይ ዝቅተኛ ማምጣታቸውን በቅሬታ መልክ መጠየቃቸውን ገልጸው፤ ይህም የፈተናው ችግር እንዳልሆነና ተቋማቱ ራሳቸውን እንዲፈትሹ የሚያስገድዳቸው ነው ብለዋል።
በቀጣይ “ደረጃውን ለጠበቀ የፈተና ከምችት” የፈተና ባንክ እንደሚያቋቁም ትምህርት ሚንስቴር አስታውቋል።