ኢትዮጵያን ከሱዳን የሚያገናኘው የመንገድ ግንባታ በይፋ ተጀመረ
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከዱርቤቴ - ቁንዝላ - ሻሁራ - ፍንጅት የሚሰራ የመንገድ ፕሮጄክትንም አስጀምረዋል
መንገዱ ከገለጎ - መተማ የሚገነባ ሲሆን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ ዛሬ አስጀምረውታል
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአማራ ክልል ከ5 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የሚገነቡ ሁለት መንገዶች ግንባታን ዛሬ ረፋድ አስጀምረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአካል ያስጀመሯቸው መንገዶች በአማራ ክልል ከዱርቤቴ - ቁንዝላ - ሻሁራ - ፍንጅት እንዲሁም ከገለጎ - መተማ መንገዶች ግንባታ ሲሆኑ 261 ኪሎ ሜትር ርዝመት አላቸው ተብሏል።
መንገዶቹ ከ5 ቢሊዮን 374 ሚሊዮን ብር በላይ ወጪ የሚፈጁ ሲሆን መንገዶቹ በሁለት ምዕራፍ እንደሚገነቡ በማስጀመሪያ ፕሮግራሙ ላይ ተገልጿል።
በአስፋልት ኮንክሪት ደረጃ የሚገነቡ ሲሆን ግንባታውን የቻይናው ዚዢያንግ ኮሚዩኒኬሽን ኮንስትራክሽን ግሩፕ በ3 ዓመት ውስጥ ለመስራት ውል ገብቷል።
መንገዱ የአማራ ክልል 3 ዞኖችን ከማስተሳሰር ባለፈ የሀገሪቱ የገቢና ወጪ ምርት ዋና መስመር የሆነውን የመተማ ሱዳን ኮሪደርን የሚያገናኝ በመሆኑ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ተናግረዋል።
የህብረተሰቡ የረጅም ጊዜ ጥያቄ የነበረው የዱርቤቴ-ገላጎ-መተማ መንገድ በምርታማነትቱ ለሚታወቀው ምዕራብ አቸፈር ወንድዬ እና ለጎንደር አካባቢ ጠቀሚታው ከፍተኛ ስለመሆኑ ያነሱት ደግሞ የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ አገኘሁ ተሻገር ናቸው።
የወሰን ማስከበር ጉዳይ ለፕሮጀክቱ ስኬት እንቅፋት እንዳይሆን ጠንክረው እንደሚሰሩ በአካባቢው ህብረተሰብ ስም ቃል ገብተዋል።
የኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ኢንጂነር ሃብታሙ ተገኘ በበኩላቸው መንገዱ ለነባሩ ከአዲስ አበባ-ባህርዳር-ጎንደር-መተማ መንገድ እንደ አማራጭ ሆኖ የሚያገለግል ከመሆኑም ባሻገር ለምዕራብ አቸፈር እና ለጎንደር ህዝብ ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ለውጥ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ያበረክታል ብለዋል፡፡
ፕሮጀክቱ በተቀመጠለት የጊዜ ገደብ ተጀምሮ እንዲጠናቀቅ የህብረተሰቡ ድጋፍ ወሳኝ በመሆኑ የአካባቢው የመስተዳድር አካላትና ነዋሪዎች አስፈላጊውን ትብብር እንዲያደርጉ ጠይቀዋል።
ይህ መንገድ ተጠናቆ ለህዝቡ አገልግሎት መስጠት ሲጀምረ ዘርፍ ብዙ ጠቀሜታ ይኖረዋል፡፡
በተጨማሪም የገቢ ወጪ ዋና መስመር የሆነዉን መተማን ከሱዳን ጋራ በማገናኘት የሁለቱን ሃገራት የንግድ ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ትስስርን የበለጠ ያጠናክራል፡፡
ከዚህም ባሻገር በዋነኛነት ነባሩን የደብረማርቆስ-ባህርዳር ጎንደር-አዘዞ-መተማ መንገዶችን ያስተሳስራል።
በግንባታ ማስጀመሪያ መርሐ ግብሩ ላይ ሌሎች የፌደራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች እና የአካባቢው ነዋሪዎች መገኘታቸውን ጠቅላይ ሚኒስትሩ በትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል።